ቤተክርስቲያኗ በመላ አገሪቱና በውጭ አገራት የሠላምና የአንድነት ስምሪት ልታካሂድ ነው

63
አዲስ አበባ ታህሳስ 4/2011 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በመላ አገሪቱና በውጭ አገራት የሠላምና የአንድነት ስምሪት ልታካሂድ ነው። የሠላምና የአንድነት ስምሪቱ የቤተ-ክርስቲያኒቷ መሪዎች፣ አገልጋዮችና ምዕመናን የሚሳተፉበት ሲሆን ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ይጀመራል። የስምሪቱ ዓላማ ሠላምን በመስበክ በአገሪቷ እየተከሰቱ ያሉ የመገዳደል ፣ ወገንን የማፈናቀል፣ እርስ በርስ የመጋጨትና የመለያየት እኩይ ተግባራትን በማስቆም ሠላምና አንድነት እንዲሰፍን ማስቻል ነው። የጠቅላይ ቤተ-ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ “ኢትዮጵያዊያን በአገራቸውም ይሁን በውጭ አገራት የሚታወቁት በርህራሄያቸው፣ በሉዓላዊነታቸው፣ በአንድነታቸው፣ በፍቅራቸውና በአብሮነት ጥበባቸው ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ “ጊዜ የወለደው ባእድ አስተሳሰብ ባሳደረብን ተጽእኖ ከምንታወቅበትና ለዓለም ምሳሌ ከሆንበት ማንነታችን በተቃራኒ አገራችን የብጥብጥና የሁከት ዜና የሚሰማባት እየሆነች መምጣቷ ይስተዋላል” ብለዋል። ሠላምና አንድነትን የሚያጠፉና የህዝቡን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚያውኩ ተግባራት መበራከታቸውንም ገልጸዋል። በመሆኑም ቤተክርስቲያኗ ትክክለኛውን የሠላም መንገድ በመያዝ ለሠላምና ለአገር አንድነት ብሎም ህዝቡን ለማረጋጋት ትሰማራለች። የፌዴራሉና የክልል መንግስታት እንዲሁም የየአካባቢው አስተዳደሮች ምትክ ለሌለው ሰላም በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል። የሃይማኖት አባቶችም በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ዘወትር ስለ ሰላም ማስተማርና መምከር፣ ግጭት ሲፈጠር ከማውገዝና የአቋም መግለጫ ከማውጣት ባሻገር አንድነትን፣ መረጋጋትን፣ እርቅና መከባበርን በማስረጽ ‘ሃላፊነታችንን መወጣት አለብን’ ብለዋል። “ስለ ሠላም መስፈን መንፈሳዊና ማህበራዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታችንን ለመወጣት፤ ዛሬ የዘራነው የሠላም ዘር ነገ ለአገራችንና ለህዝቦቿ መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ቤተክርስቲያኗ የሰላምና የአንድነት መድረክ ለማካሄድ ተዘጋጅታለች” ነው ያሉት። ስምሪቱ ከታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ከአህጉረ ስብከት እስከ አጥቢያ ድረስ የሚዘልቅ፣ በሠላምና በአንድነት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትምህርትና ስልጠና የሚሰጥበትና ውይይቶችም የሚካሄዱበት ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም