የሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ወታደሮች አንዳቸው የሌላቸውን ድንበር በወዳጅነት መሻገር ጀመሩ

66
ታህሳስ 4/2011 የሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ወታደሮች አንዳቸው የሌላቸውን ድንበር በወዳጅነት መሻገራቸው የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ስቧል። ወታደሮቹ ሁለቱ ሀገራት ከተከፋፈሉ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው አንዱ የሌላውን ድንበር በወዳጅነትና በሰላም የተሻገሩት ተብሏል። በድንበር አካባቢ የነበሩ ወታደራዊ ጣቢያዎች እየፈረሱ መሆኑን እንዲቃኙ ተልዕኮ የተሰጣቸው የሁለቱም ሀገራት ወታደሮች ድንበር ተሻግረው ሰላምታ ሲለዋወጡ አብረው ሲንቃቀሱ የሚያሳዩ ምስሎችም ተለቀዋል። ከ1950ዎቹ የኮሪያ ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ ልሳነ ምድሩ ከሁለት ተከፍሎ ሁለቱ ሀገራት በባላንጣነት ሲተያዩ ቆይተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን ለማሻሻልና የወዳጅነት ትስስር ለማጠናከር ጥረት ጀምረዋል። የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ሙን ጄ ኢን ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር እየተገናኙ ወይይት እያደረጉ ናቸው። ከውይይታቸው ውስጥ ሁለቱ ሀገራት በድንበሮቻቸው ያሉትን የተጠንቀቅ ወታደራዊ ጣቢያዎች ማፍረስ ጉዳይ ይገኝበታል። ከህዳር ወር ጀምሮ 10 ወታደራዊ ጣቢያዎቻቸውን ማንሳታቸውም ይታወቃል። በትናንትናው ዕለትም የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልዑክ የሰሜን ኮሪያን ወታደራዊ ጣቢያ መፍረሳቸውን የሚያረጋግጥ ቅኝት አድርጓል። በተመሳሳይ የሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ልዑኮችም የደቡብ ኮሪያን የድንበር ወታደራዊ ጣቢያ የማፍረስ ሂደት ቃኝተዋል። ምንጭ፦ቢቢሲ  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም