የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ወቅታዊ ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ ሊሻሻል ይገባል - ምሁራን

71
አዲስ አበባ  ታህሳስ 3/2011 የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ወቅታዊ የሆኑ ውስጣዊና ውጫዊ ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ ሊሻሻል እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሥራ ላይ ከዋለ 16 ዓመታትን አስቆጥሯል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ፈቃደ ተረፈ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጊዜውን፣ ዘመኑንና አዳዲስ ክስተቶችን በሚመጥንና ምላሽ በሚሰጥ መልኩ 'ሊሻሻል ይገባል' ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ለ16 ዓመታት ሲተገበር የሀሳብና የመርህ ለውጥ ያላሳየ ሲሆን ዋነኛ ትኩረቱም በአገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ ነው። እንደ ዶክተር ፈቃደ ገለጻ መንግስት በሥራ ላይ ያለውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲያወጣ ትኩረት ያደረገው በውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ በመሆኑ ማሻሻያ ሲደረግ ምላሽ የሚሹ አዳዲስ ውጫዊ ጉዳዮችን ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል። የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ መንግስት አገር ወክለው በውጭ አገር የሚመደቡ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ሹመት ላይ እውቀትና ክህሎትን መሠረት ያደረገ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ታፈሰ ኦሊቃ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቢሮክራሲ የላትም ይላሉ። 'የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቢሮክራሲን የማሻሻል ሥራ ለነገ የሚተው ጉዳይ አይደለም' ያሉት ዶክተሩ በአምባሳደርነት የተመደቡ ሰዎች ብቃትና እውቀት 'ሊፈተሽ ይገባል' ነው ያሉት። በተለይ መንግስት በውጭ ጉዳይ ላይ አቅዶ መስራት የሚችለው ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አገልግሎትና በዘርፉ የሚመደቡ ባለሙያዎች እውቀትና ክህሎት በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ሲገኝ ብቻ እንደሆነም አብራርተዋል። ኢዜአ በአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎችን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ቢጠይቅም ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። በሌላ በኩል የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ በ59 ሚሲዮኖችና በዋናው መስሪያ ቤት አዲስ የሰራተኞች ድልድል አካሂዷል። በቅርቡ የመስሪያ ቤቱን ዲፕሎማቶችና ሌሎች ምሁራንን ያማከለ የአምባሳደሮች ምደባ እንደሚካሄድም ይፋ አድርጓል። የተቋሙን ዲፕሎማቾችና ምሁራንን የሚያማክለው የአምባሳደር ድልድልና ምደባ ሙያዊ ክህሎትና እውቀትን መሰረት አድርጎ እንደሚከናወን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በሰጡት መግለጫቸው ጠቁመዋል። የድልድሉ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለውጥ የሚደግፉ ውጤታማ ዲፕሎማቶች መፍጠር እንደሆነም አቶ መለስ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ባሏት 59 ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች 412 ዲፕሎማቶች አሏት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም