በሐረር የትራፊክ መንገድ መብራት ብልሽት የትራፊክ አደጋዎችን አባብሷ

60
ሐረር ታህሳስ 3/2011 በሐረር ከተማ የትራፊክ መብራት ባለፉት ስምንት ወራት ሥራ በማቆሙ እየተከሰተ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የክልሉ መንግሥት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠው እግረኞችና አሽከርካሪዎች ጠየቁ። መብራቱ በቀን ከ20 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ፍሰትን ያስተናግዳል። የመንገዱ ተጠቃሚዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት በከተማዋ ማዕከላዊ ሥፍራ የተተከለው መብራት ባለፈው ዓመት አገልግሎት በመቋረጡ አደጋዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። የሐረሪ ክልል መንግሥት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መፍትሄ ሊፈለግለት ብለዋል። አቶ ረዘነ ባህረጽዮን የተባሉ  አሽከርካሪ መብራቱ ከአራት አቅጣጫዎች የሚመጡ ተሽከርካሪዎችን ስለሚያስተናግድ የትራፊክ መጨናነቅ እንደሚፈጠር ገልጸው፣ በየጊዜው እየደረሰ ያለው የሰውና የንብረት ላይ ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። የመብራቱ ብልሽት አሽከርካሪዎች ሕግና ሥርዓት ተከትለው ሳይሆን በግዴለሽነት እንዲያሽከረክሩ አድርጓል ያሉት ሌላው የባለ ሦስት እግር አሽከርካሪ አቶ ደሳለኝ መኩሪያ ናቸው። አቶ ጋሻው ነጋሽ የተሰኙ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው መብራቱ እግረኛና ተሽከርካሪ ተናበው ይስተናገዱበት የነበረውን ሁኔታ በማስቀረቱ አደጋዎች እየተበራከቱ መጥተዋል ይላሉ። የታክሲ አሽከርካሪው ወጣት ቴዎድሮስ እጅጋየሁ በሰጠው አስተያየት መብራቱ ሥራ በማቆሙ  አሽከርካሪዎች እርስ በርሳቸው መሽቀዳደምና ሥርዓተ አልበኝነት እንዲነግስ ማድረጉን ይናገራል። ለአብነትም ለአምቡላንስ እንኳን ቅድሚያ እንደማይሰጥ ተናግሯል። የክልሉ መንግሥት በከተማው ብቸኛ የትራፊክ መብራት ወደ አገልግሎት እንዲመለስ ሊያደርግ ይገባል ብሏል። የክልሉ የትራፊክ ፖሊስ ዋና ሳጅን ከድር አብዱሰላም ችግሩ የትራፊክ ፍሰቱን ለመቆጣጠር አዳጋች እንዳደረገው ይናገራሉ።ካለመንጃ ፈቃድና ሠሌዳ ቁጥር የሚያሽከረክሩ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኗብናልም ሲሉም ችግሩን ያሳያሉ። ችግሩን ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አመልክተዋል። የክልሉ ትራፊክ ፖሊስ የአደጋ ምርመራ ክፍል ሪፖርት እንደያመለክተው መብራቱ ሥራ ባቆመባቸው ወራት 30 የትራፊክ አደጋዎችን ተስተናግደዋል፤በዚህም በ12 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሷል። የሐረሪ ክልል መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ደህንነት ባለሙያ እንደሚናገሩት አቶ መሐመድ ዑመር ለትራፊክ መብራት ችግር በአስቸኳይ መፍትሄ ለመስጠት ያልተቻለው የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅቶ ባለመስራታቸው ነው። በአሁኑ ወቅት  መብራቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመቀየር ጨረታ መውጣቱንና ሥራውንም በአምስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በብልሽት የቆመውን መብራት ጥገና በማድረግ  ወደ ሥራ ለማስገባት እንቅሰቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም