በብዙ የአገሪቱ ስፍራዎች ደረቃማው የአየር ሁኔታ ሰፍኖ ይቆያል

57
አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2011 በሚቀጥሉት አስር ቀናት በብዙ የአገሪቱ ስፍራዎች ደረቃማው የአየር ሁኔታ ሰፍኖ እንደሚቆይ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተለይም በደጋማ የአገሪቱ አካባቢዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ሊጠናከር እንደሚችል ይጠበቃል። በሌላ በኩል በጥቂት የምዕራብና የደቡብ ኦሮሚያ፣  የደቡብ ክልል፣ እንዲሁም በሰሜንና በደቡብ ወሎ ዞኖች አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ጠቁመዋል ብሏል ኤጀንሲው። በመሆኑም የሚጠበቀው ደረቃማ የአየር ሁኔታ በመከናወን ላይ ለሚገኘው የሰብል ስብሰባና ድህረ ሰብል ስብሰባ እንቅስቃሴ በጎ ጎን እንደሚኖረው ጠቁሟል። በሌላ በኩል ከደረቃማው የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ደጋማ አካባቢዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቅቃዜ ሊጠናከር እንደሚችል የተተነተኑ የትንበያ መረጃዎች አመላክተዋል። ይህም ሁኔታ በተለይም በመስኖ በመታገዝ በሚለሙ አትክልቶች፣ የፍራፍሬ ተክሎችና ቋሚ ሰብሎች እንዲሁም በእንስሳት ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው ስለሚችል አስፈላጊውን ዝግጅትና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብሏል። አነስተኛ መጠን ያለው እርጥበት ሊኖራቸው እንደሚችል በተጠቀሱት ጥቂት የምዕራብና የደቡብ ኦሮሚያ፣ የደቡብ ክልል የሚጠበቀው እርጥበት ለሚያከናውኑት የእንስሳት ልማት፣ ለሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች አዎንታዊ ጎን ይኖረዋል። በሌላ በኩል የዝናብ ወቅታቸው ባልሆነው የሰሜንና የደቡብ ወሎ ዞኖች የሚጠበቀው አነስተኛ እርጥበት በሰብል ስብሰባና በድህረ ሰብል ስብሰባ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው ስለሚችል አርሶ አደሮች ይህን ምቹ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የደረሱ ሰብሎችን በጊዜ እንዲሰበስቡም መክሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም