ኢትዮጵያና እስራኤል በጋራ ለመስራት መከሩ

157
አዲስ አበባ ሚያዚያ 24/2010 ኢትዮጵያና እስራኤል በልማትና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት በሚያስችላቸው ሁኔታ መከሩ። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙትን የእስራኤል አቻቸውን ሬዩቪን ሪቭሊን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። የሁለቱ አገራት መሪዎች ከውይይታቸው በኋላ በጋራ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ እንደተናገሩት የኢትዮጵያና እስራኤል የትብብር ግንኙነት ወደ ሶስት ሺህ ዓመታት የሚጠጋ በንጉስ ሰለሞንና ንግስት ሳባ ወቅት የተጀመረ ነው። በምክክራቸው ወቅትም በልማትና ጸጥታ ጉዳዮች አብረው መስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ነው የተናገሩት። ይህንን የቆየ ግንኙነት በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ግብርናና ሌሎች የልማት ዘርፎች ወደላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚፈልጉ ነው የገለጹት። እንደ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ገለጻ በሁለቱ አገራት መካከል የትብብር መስኮችን ለማጠናከርና መግባባት ላይ ለመድረስ ፕሬዝዳንት ሪቭሊን ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ታሪካዊ ያደርገዋል። እስራኤል ኢትዮጵያ ለምትሰራቸው ዋና ዋና የልማት ፕሮጀክቶች የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንድታደርግም ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል። የሁለቱን አገራት ተጠቃሚ በሚያደርጉ የኢንቨስትመንት ዘርፎችና በተለያዩ የልማት ዘርፎች ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል። በተጨማሪም በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በቴክኒክ ትብብር፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ግብርናን በማዘመንና በሌሎች የልማት ዘርፎች በጋራ በመስራት አገራቱ ያላቸውን አቅም መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል። የእስራኤል ፕሬዝዳንት ሮቨን ሪቭሊን በበኩላቸው በውሃ፣ በቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በግብርና፣ ምግብ ዋስትና፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ሳይበርና ሌሎች የልማት ዘርፎች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት በምንችልበት ሁኔታ ላይ መክረናል ብለዋል። የጉብኝታቸው ዓላማ በሁለቱ አገራት ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር የተሻለ ነገን ለህዝቦች ለመፍጠር መሆኑንም ጠቅሰዋል። የዓለም ፈተና በሆነው ሽብርተኝነት ላይም ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደሚፈልጉ ፕሬዝዳንት ሪቭሊን ገልጸዋል። "ኢትዮጵያን በመጎብኘቴ ኩራት ይሰማኛል" በማለት የሁለቱ አገራት ህዝቦች ወደፊት አሁን ካለው በተሻለ ግንኙነታቸው እንደሚዳብር እምነታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያና እስራኤል ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1956 ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም