የላቦራቶሪ አገልግሎት የተሟላ አለመሆን ለተጨማሪ ወጪና እንግልት ዳርጎናል

132
ታህሳስ 3/2011 ከተለያዩ አካባቢዎች በሪፌራል ወደ አዲስ አበባ ሆስፒታሎች የሚላኩ ህሙማን የተማላ የላቦራቶሪ አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ በሆስፒታሎቹ የማይሰጡና የተቋረጡ ላብራቶሪ አገልግሎቶችን በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት  በማሰራት ህሙማኑን ከእንግልትና ከወጭ ለማዳን ቢሰራም  በሁለቱም ተቋማት የማይገኙትን ወደ ግል የህክምና ተቋማት እንደሚልኩ ነው ያናገርናቸው  ሆስፒታሎች መረጃ የሚያሳየው። ሆስፒታሎቹ ይሄን ይበሉ እንጂ ረጅም ርቀት ተጉዘው ወደ ሆስፒታሎቹ ብመጡም አብዛኛውን የላቦራቶሪ አገልግሎት ወደ ግል የህክምና ተቋማት በመላካቸው ለተጨማሪ ወጪና እንግልት እንደተጋለጡ ህሙማኖች ይናገራሉ። ወጣት ዘይነባ ያሲን አክስቷን ለማስታመም ከጅማ ሶኮሮ ወረዳ በሪፈር ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ብትመጣም ከታዘዘላት ሶስት አይነት የደም ምርመራ ሁለቱን ውጪ ማሰራቷን ተናግራለች፡፡ በዚሁ ሆስፒታል እህቱን ለማስታመም ከአምቦ መምጣቱን የተናገረው  ወጣት ሙሀመድ ነስሮ ከተማውን በደንብ ባለማወቁ ወደ ውጭ የታዘዘውን የላብራቶሪ ምርመራ ለማሰራት  መንገላታቱን አስረድቷል፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ  ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር ወንድማገኝ ገዛህኝ እንዳሉት ሆስፒታሉ 104 የላቡራቶሪ  ዓይነቶች  አገልግሎት መስጠት ስገባው   የላብራቶሪ መሳሪያዎች ግዥ በወቅቱ ባለመፈፀሙ ስድስት የላቦራቶሪ አገልግሎቶች በሆስፒታሉ አይሰጥም፡፡ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ  የጉበት ህክምና የምትከታተለው ዙፋን አለማየሁ “የበሽታዬ አይነት ተደጋጋሚ ምርመራና ውጤት የሚጠይቅ በመሆኑ ከሆስፒታሉ ውጪ በሚሰሩ ምርመራዎች ለወጪ ተዳርጌያለሁ” ነው ያለችው፡፡ በፅኑ ህሙማን ክፍል የተኙ ዘመዳቸውን በየካቲት 12 ሆስፒታል እያስታመሙ  መሆናቸውን የነገሩን ወይዘሮ ገነት ከበደ አብዛኛውን የላብራቶሪ ምርመራዎች በግል ህክምና ተቋም እንደሚያሰሩና የደም ናሙና መውሰጃ  እቃዎችና ጓንት  ሳይቀር “የለም” እንደሚባሉም ነው የገለፁት። የሆስፒታሉ የላብራቶሪ ክፍል አስተባባሪው አቶ ዳንኤል መልካሙ ስለጉዳዩ ተጠይቀው    አሁን ባለው ሁኔታ  85 የላቦራቶሪ  ናሙናዎችን መስራት ቢጠበቅበትም በላቦራቶሪ ማሽን እጥረት 67ቱን ብቻ  እየሰሩ መሆኑን  ነው የጠቀሱት። ወ/ሮ ለዝና ባህሩ አባታቸውን የደም ካንሰር ለማሳከም ከደሴ በሪፈር ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቢመጡም ወረፋ በመጠበቅ ብቻ ሳምንት አስቆጥረው ላቦራቶሪ  ቢታዘዝላቸውም አገልግሎቱን ባለማግኘታቸው ውጭ በማሰራት ከፍተኛ ውጣውረድ እንደገጠማቸው ይናገራሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሪፌራል ሆስፒታል የስኳርና የልብ ህመም ክትትል እንዳላቸው  የጠቀሱት ወ/ሮ ሙሉነሽ ሞገስ  በሆስፒታሉ ከታዘዘላቸው ሶስት የላብራቶሪ ናሙና ሁለቱን በውስጥና አንዱን ውጭ ማሰራታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል የዲያጎናስቲክ ክፍል ኃላፊ ዶክተር ምህረቱ መሀሪ እንዳሉት ሆስፒታሉ  138 የላቦራቶሪ ናሙናዎችን አገልግሎት መስጠት ስገባው 76ቱን ብቻ በውስጥ በመስጠት፤ 15 ናሙናዎችን ፓስተር በመላክና 47 አይነት የላቦራቶሪ ናሙናዎችን  ህሙማኑ በውጭ የጤና ተቋማት ያሰራሉ። በላቡራቶሪ እቃዎች ብልሽትና የኬሚካሎች እጥረት የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ በማስተጓጎል ለህሙማኑ የሚሰጠው ተደጋጋሚ ቀጠሮ ጤናቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማድረሱንም ገልጸዋል፡፡ በአብነትም በግብአት እጥረት ያለ አገልግሎት የተቀመጠ የሂማቶሎጂይ ማሽን መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ የአንድ ሰው መታመም ቤተሰብን ጭምር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያጋልጥ መሆኑን ያስረዱት ዶክተር ምህረቱ በተለይም አብዛኛው ህሙማን ከክፍለ ሀገር የመጡ በመሆናቸው ለላቦራቶሪ  አገልግሎት ወደ ውጭ መላካቸው ከተማዋን ባለማወቅ ከሚደርሰው መጉላላት ባሻገር የገንዘብ  ብክነት ማስከተሉንም ተናግረዋል፡፡ በፌደራል መድሀኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ አድና በሬ ስለ ላቦራቶሪ ግብዓት አቅርቦት የተነሳውን ቅሬታ ተጠይቀው ኤጀንሲው ዋና ዋና የህክምና መሳሪያ፣ የመድሀኒት፣ የላብራቶሪ ሪኤጀንት እና ማሽን ለጤና ተቋማት  ለማቅረብ መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡ በበጀት አመቱም የጤና ተቋማት ያቀረቡትን የግዥ ፍላጎት መሰረት በማድረግ 1ሺ373 አይነት የህክምና መገልገያ፣ መድሀኒትና  የላቦራቶሪ ግብአት ለመግዛት ዝርዝር መለየቱን ነው ያስረዱት፡፡ የህክምና ግብአት እጥረትና በወቅቱ አለመቅረብ ችግር የተከሰተው የጤና ተቋማቱ የግዥ  ፍላጎታቸውን  በመረጃ ባለመለየታቸው ነው  ያሉት ፡፡ በግብአት እጥረት ያለ አገልግሎት የተቀመጠ የሂማቶሎጂ ማሽን ስለ መኖሩ ለተነሳው ቅሬታ ኤጀንሲው ለገዛቸው 54 ማሽኖች ብቻ ሪኤጀንት ቢገዛም ተቋማቱ በራሳቸው ለገዙዋቸው ከ100 በላይ ማሽኖችን  ጥቅም ላይ ለመዋል  እጥረት መከሰቱን ገልጸዋል፡፡ ለአቅርቦት መቆራረጥ የትንበያ ጥራት ብቻ ሳይሆን ኤጀንሲው ለሚያወጣው  አለም አቀፍ ጨረታ አቅራቢዎች ለአነስተኛ ግዥ ያለመሳተፋቸው ተደጋጋሚ ጨረታዎች እንዲወጡ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ ኤጄንሲው ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት አቅራቢዎች ማሽኑን በነጻ ሰጥተው ከ90 በመቶ በላይ ቅናሽ በሆነ ዋጋ ሪኤጀንት የሚያቀርቡበትን የሶስት አመት ውል መፈረሙን አስረድተዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም