የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል የኑሮ ውድነቱን እንዳባባሰባቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

122
አሶሳ ታህሳስ 3/2011 ከአሶሳ ወደ አዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎል የእህልና የሸቀጦችን ዋጋ በመጨመር የኑሮ ውድነቱን  እንዳባባሰው የአሶሳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች በተከሰተ የጸጥታ ችግር የአሶሳ-አዲስ አበባ መንገድ በተደጋጋሚ ይቋረጣል፡፡ አንዳንድ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት ችግሩ በአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና አሳድሯል፡፡ በተለይ ሰሞኑን በከተማው የእህልና የሸቀጦች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቶበታል፡፡ ለአብነትም የአንድ ኪሎ ግራም ጤፍ ዋጋ ከ25 ብር ወደ 40 ብር፣ የዳቦ ዱቄት ከ20 ብር ወደ 25 ብር፣ የሽንኩርት ዋጋ ከ10 ብር ወደ 30 ብር ከፍ ማለቱን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል፡፡ ችግሩ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ  ላይ የሚገኙ ቤተሰቦችን ሕይወት አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል፡፡ አንዳንድ ነጋዴዎች በመጋዘን ያከማቹትን እህልና ሸቀጦች ሰሞኑን የገቡ አስመስለው ዋጋ ጨምረው በመሸጣቸው ኑሮ እንዲወደድ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ አብዱ ካሳው የተባሉ አስተያየት ሰጪ መንግሥት መንገድ የሚዘጋባቸውን ምክንያቶችን በመመርመር መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንግድና ዘርፉ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የአሶሳ -አዲስ አበባ መንገድ በመዘጋቱ ሸማቹ ብቻ ሳይሆን ነጋዴውም ተጉላልቷል ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ችግሩን ለማቃለል የአገር ሽማግሌዎችን ወደ ምዕራብ ወለጋ በመላክ ከ40 የሚበልጡ ተሸከርካሪዎች ሸቀጦች ይዘው እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የንግዱ ማህበረሰብ የመንገዱን መዘጋት አሳብቦ ያለአግባብ ዋጋ ጭማሪ አድርጓል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸው፣ በዚህ ዓይነት ተግባር  የተሰማሩ ነጋዴዎች መኖራቸው ከተደረሰበት ምክር ቤቱ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አልማሂ ቢሮው ችግሩን ለመፍታት ሁለት አማራጮችን እየተከተለ መሆኑን ይናገራሉ። አንድም ከአሶሳ በመተከል ወደ አዲስ አበባ የሚወስደውን መንገድ መጠቀም ይሆናል። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉት ነጋዴዎች  ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡ እጥረቱ በአሶሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎችና በአጎራባች ኦሮሚያ ክልልም እንደሚታይ አመልክተዋል። ለችግሩ ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት የቀረበውን መንገድ ተጠቅመው ሸቀጦችን የሚያቀርቡ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ቢሮው ጭማሪው እንዳይጋነን የቅርብ ክትትል ያደርጋል ብለዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከኦሮሚያ ክልልና ከፌዴራል መንግሥት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም