በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው

111
ታህሳስ 3/2011 በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ውስጥ ሴቶች የህዝቡ ጠንካራ አካል መሆናቸውን በተጨባጭ እያረጋገጡ ነው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገሳ ተናገሩ፡፡ አራተኛው የኦዴፓ ሴቶች ሊግ ጉባኤ “የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማፋጠን እኛ ሴቶች በቁርጠኝነት እንሰራለን” በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገሳ ባስተላለፉት መልእክት ሴቶች የህብረተሰቡ ትልቁ አካል ቢሆኑም በሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ በፖለቲካ፣በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የነበራቸው ተሳትፎ አነስተኛ ነው፡፡ ነጻ የወጣ ዜጋን ለማፍራት እንደ ህዝብ ትግል ተደርጎ በመጣው ለውጥ ውስጥ የሴቶች መብት እንዲከበር በማድረግ ተሳታፊነታቸውና ተጠቃሚነታቸው እየጨመረ መቷል ብለዋል፡፡ አቶ ለማ እንዳሉት “በተለይ እየተካሄደ ባለው ሪፎርም ውስጥ ፓርቲያችን ባደረገው ጠንካራ ትግል ሴቶችን የስልጣን ባለቤት በማድረግ ተጨባጭ ስራ ተሰርቷል”፡፡ ኦዴፓ ሴቶችን አሁን ለደረሱበት ትልቅ ኃላፊነት እንዲደርሱ ያደረገው ትግል ክፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ “ዛሬ እንደ ፓርቲያችን አሁን የታየውን ለውጥ ለማየታችን የሴቶች ድርሻ ከፍተኛ ነው፤ስለዚህ ደግሞ ትልቅ ምስጋና አላቸው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡ ሴቶች የፓርቲው ጉልበት በመሆናቸው የሴቶቹን አደረጃጀት ማጠናከር ወሳኝ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ እስካሁንም ጠንካራ አደረጃጀት የሴቶች ሊግ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡ የኦዲፓ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበር ወይዘሮ ቆንጅት በቀለ በበኩላቸው ሊጉ ባለፉት ዓመታት በሀሉም መስክ የሴቶችን አቅም የመገንባት ስራ ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም በማህበራዊና ኢኮኖሚ መስክ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመው በተለይ በውሳኔ ሰጪነት የሴቶች ተሳትፎ ማደጉን አመልክተዋል። ሊጉ እስከ ነገ በሚቆየው ጉባኤው  የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸምን በመገምገም በቀጣይ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲሁም በኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደር ችግሮችና መፍትሄያቸው  ዙሪያ እንደሚመክር ሊቀመንበሯ  አስረድተዋል። የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ  ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተው ሊጉን በቀጣይ ሁለት  ዓመት ተኩል  የሚመሩ እንደሚመረጡም ጠቁመዋል። በጉባኤው መክፈቻ ስነ-ስርዓት የእህት ብሔራዊ ደርጅቶች ሴቶች ሊጎች ተወካዮች ድጋፋቸውን በመግለጽ የኦዲፓ ሴቶች ሊግ በቀጣይ በሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም