የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የካንሰርና የልብ ህክምና ማእከል ግንባታ 56 በመቶ ደርሷል

75
ታህሳስ 3/2011 የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከ986 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚያስገነባው የካንሰርና የልብ ህክምና ማእከልን በተያዘለት ግዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተገለጸ። የሆስፒታሉ የምህንድስና ኢንጂነሪንግ ክፍል ሱፐር ቪዥን ኢንጅነር ሞቲ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት እየተገነቡ ያሉት የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከሎች መጀመሪያ አካባቢ ቶሎ ወደ ሥራ ያለመግባትና በብረት ዋጋ ንረት ምክንያት መዘግየት የታየበት ቢሆንም ግንባታው 56 በመቶ  ደርሷል፡፡ የማእከላቱ መሰረት በ12 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ባለ12ና 10 ወለል ህንፃዎች ይኖሩታል ብለዋል።   ህንፃዎቹ ከ600 በላይ የመኝታ ክፍሎች እንደሚኖራቸው ነው ኢንጂነር ሞቲ ያብራሩት፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከተጀመረ ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረውና ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የእናቶችና ህጻናት ማዕከል ባለ 8 ወለል ህንፃም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ   ተናግረዋል፡፡ በኮንትራክተሩና ክትትል በሚያደርገው ተቆጣጣሪ ድክመት ምክንያት ተጓቶ የነበረው ፕሮጀክቱ ባለሙያዎችን በመቀየር  በአሁኑ ወቅት ስራው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝና በዚህ ሳምንት ከፊሉን  ስራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል። የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ሜዲካል አገልግሎት  ዋና ፕሮቮስት ዶክተር ወንድማገኝ ገዛህኝ በበኩላቸው ማዕከላቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በሀገሪቱ በካንሰርና በልብ ህመም ለሚሰቃዩ ዜጎች የሚሰጡት ጥቅም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ ህክምናዎቹ የሚጠይቁት ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ አብዛኛውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ  ያደርጋል ነው ያሉት። ከ7 ዓመት በፊት ሆስፒታሉ በቀን ከ500 ያልበለጡ ህሙማንን ብቻ ያስተናግድ  እንደነበር  የተናገሩት ዶክተር ወንድማገኝ ፤በአሁኑ ወቅት  በየቀኑ ለ2 ሺህ ሰዎች ህክምና እንዲሁም ነው ብለዋል፡፡ በአሁኑ በወቅት በወር ለ1 ሺህ 500 እናቶች የወሊድ አገልግሎት እየተሰጠ ሲሆን በግንባታ ላይ የሚገኘው የእናቶችና ህፃናት ህንፃ ሲጠናቀቅ በቀን ለ400 እናቶች የወሊድ አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ህንፃው 15 የማዋለጃ ክፍሎች እንደሚኖሩት የጠቀሱት ዶክተር ወንድማገኝ በቅርቡ አገልግሎቱን ለማስጀመር ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል። የሆስፒታሉ ሀኪም ዶክተር ዮናስ ገብረጊዮርጊስ በበኩላቸው የሚገነቡት የካንሰርና የልብ ህክምና ማዕከላት በሀገሪቱ በመንግስት በብቸኝነት አገልግሎት እየሰጠ ካለው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተጨማሪ በመሆን ህብረተሰቡ የጤና አገልግሎቱን በአቅራቢያው እንዲያገኝ ያስችላል ብለዋል፡፡ የማእከላቱ መገንባት በሀገሪቱ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣውን የካንሰር ህመም ለመከላከል የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ዮናስ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ፕሮጀክቱ በ2 አመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም   ተነግሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም