በዩኒቨርሲቲዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት የአምስት ተማሪዎች ህይወት አልፏል

108
አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2011 በቅርቡ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በግለሰቦች ደረጃ ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት የቡድን መልክ በመያዝ ወደሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተዛምቶ የአምስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየመከሩ ናቸው። በምክክር መድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ናቸው። ምክክሩ ሲጀመር የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም እንደተናገሩት፤ በዩኒቨርሲቲዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ለሰው ህይወት መጥፋት ጭምር የዳረገ ጉዳት ደርሷል። በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ በግለሰቦች ደረጃ የተፈጠረ አለመግባባት ወደ ቡድን መልክ በመቀየር በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተዛምቶ የነገ ተስፋ የሆኑ አምስት ተማሪዎችን ህይወት ቀጥፏል ብለዋል። ችግሩን ለማርገብና ዘላቂ ሰላም  ለማስፈን ታልሞ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ግጭት ወደተከሰተባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተንቀሳቅሰው ባከናወኑት ተግባር አንጻራዊ ሰላም እንደመጣ ዶክተር ሂሩት ተናግረዋል። አሁን ባለድርሻ አካላት በሚያደርጉት ምክክር ዘላቂ የሆነ ሰላም ሊያረጋግጥ የሚችል ሃሳብ እንደሚፈልቅ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም