በአዳማ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የአስር ሰዎች ህይወት አለፈ

68
አዳማ ታህሳስ 3/2011 በምሰራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ መርመርሳ በተባለው አካባቢ ዛሬ ጠዋት  ባጋጠመው የተሽከርካሪዎች ግጭት የአስር ሰዎች ህይወት ማለፉን  ፖሊስ አስታወቀ። የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለፁት ዛሬ ጠዋት 12 ሰዓት ተኩል አከባቢ አደጋው የደረሰው ከአዋሽ ሰባት  ኪሎ ከተማ  16 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ አዳማ ሲጓዝ የነበረ ሃይሩፍ የህዝብ ማመለለሻ ተሽከርካሪ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ይጓዝ  ከነበረ ዋልያ አገር አቋራጭ የህዝበ ማመላለሻ አውቶቡስ ጋር መርመርሳ በተባለው አካባቢ በመጋጨታቸው ነው። በአደጋው በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኢት 01289 ሃይሩፍ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ ሾፌሩን ጨምሮ 9 ሰዎች ወዲያውኑ ህይወታቸውን አልፏል። በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 ኢት 97486 ዋልያ አገር አቋራጭ አውቶቡስ ውስጥ ከነበሩ ተሳታፊዎች መካከል የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ኮማንደሩ ተናግረዋል። በአደጋው ህይወታቸው ካለፈው ሌላ በአራት ሰዎች ላይ ከባድ በሶስት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክተው ተጎጂዎቹ በአዳማ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል። "የአደጋው መንስኤ አለአግባብ ደርቦ ለማለፍ መሞከርና ቅድሚያ አለመስጠት ነው" ያሉት ኮማንደር አስቻለው  የአውቶቡሱ ሾፌር ለጊዜው ባለመገኘቱ ፖሊስ ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም