የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ ቀዳሚ ሚና ሊጫወቱ ይገባል-የአከሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

68
አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ቀዳሚ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ። ሰላም ለአንድ አገር ህልውና መጠበቅና ለህዝቦቿ ደህንነት መረጋገጥ የሚያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። ሰላም ከሌለ ህጻናት እንደልብ ቦርቀው ለማደግ፣ ህዝቦች ከአንዱ ወደ ሌላው አካባቢ እንዳሻቸው ለመንቀሳቀስ፣ የእለት ጉርሳቸውን ለማዘጋጀትና ሌሎችንም የእለት ተግባራቸውን ለመከወን እንደማይችሉም እሙን ነው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት በተለይም በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አለፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች ነገ ተምሮ ቤተሰቡንና አገሩን ይጠቅማል ብሎ ልጁን ለሚልክ ወላጅም አሳሳቢና እረፍት የሚነሳ ጉዳይ ነው። በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ነገ ጥሩ ዜጋ የሚያፈሩ በመሆናቸው የሰላም መደፍረስ መንስኤ ሳይሆኑ የሰላም ምንጭ ሊሆኑ ስለሚገባቸው ተማሪዎች ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆን አለበት። በመሆኑም በየትኛውም አካባቢ የሚገኝ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ የራሱን ሃላፊነት ከተወጣ የአገራችን ሰላም አምባሳደር መሆን ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። ከዚህም ጎን ለጎን  መንግስት የተለያዩ የማህበረሰብ አካላትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በአግባቡና በወቅቱ መመለስ እንዳለበትም በመግለጽ። ሂወት ጉእሽ የ4ኛ አመት መካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ "እንደሚታወቀው ተማሪ የሚያስፈልገው እንደዋና ግብዓት ሰለም ነው፤ ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር ስለሚበላሽ መጀመሪያ ከተማሪም ከማህበረሰቡም ጸጥታን ማስከበር የመጣበትን ዓላማ ትምህርት እስከሆነ ድረስ ትምህርቱን ተከታትሎ በአግባቡ እንዲፈጸም ሰላሙ በእጃችን ስላለ በራሳችን ማስጠበቅ አለብን ብዬ አስበባለው።" ብላለች፡፡ የ3ኛ አመት የማኔጅመንት ተማሪው ሮቤል አዱኛ በበኩሉ "ሰላም ለደቂቃም ቢሆን መጥፋት መቻል የለበትም ዩኒቨርሲቲዎች የሰላም መደፍረስ መንስኤ ሳይሆን መሆን ያለባቸው ለአገራችን ሰላም መምጣት ነው መንስኤ ሊሆኑ የሚገባው ፤ ያ ማለት እንግዲህ አገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ህዝቦች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሉ ፤ መንግስት እንደ መንግስት መመለስ የሚገባውን ጥያቄዎች ከመለሰ እኛ እዚህ ያለን ልጆች ከተለያየ አቅጣጫ ስለመጣን ጥያቄዎች ከተመለሱ ምንም አይነት ግጭት ሊፈጠር አይችልም። በአግባቡ ቢመልስና አገራችን ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንድትመለስና የሰላም ተምሳሌት ብትሆን የተሻለ ነው ብዬ አስባለው።" የ2ኛ ዓመት የባዮ ቴክኖሎጂ ተማሪ ተመስገን በቀለም በበኩሉ "ተማሪዎች ማድረግ ያለባቸው ሰላም ሲኖር ነው ሁሉም ነገር የሚኖረው ስለዚህ አጠገባችን ያሉ ጓደኞቻችን ከዶርማችን ጀምረን ፍቅር ኖሮን ተቻችለን አንድ ሰው መጥፎ ድርጊት የሚያስብ ከሆነ እና በተለያዩ ምክንያቶች ሱስ ውስጥ ያሉ ተማሪዎችንም በምክርና ድጋፍ በማድረግ ፍቅርና ሰላም እንዲወርድ ማድረግ ነው።"
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም