የአክሱም ከተማ የሐይማኖት አባቶች ስለ ሰላም በማስተማር ሐይማኖታዊና አገራዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡ አረጋገጡ

49
አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2011 በየእምነት ተቋማቸው ህዝቦች ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ በማስተማር ሐይማኖታዊና አገራዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡ በአክሱም ከተማ የሚገኙ የሐይማኖት አባቶች ገለጹ። ስለ ሰላም፣ ፍቅር፣ የህዝቦች አንድነትና አብሮነት እንዲሁም ስለ መረዳዳት የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ትምህርት ይሰጣሉ። ''ይህች አገር የሰላም አገር ናት'' የሚሉት የሃይማኖት አባቶቹ፤ አገራችን የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌት ሆና ለዘመናት መኖሯን ለማስቀጠል መስራት የሚያስፈልግ መሆኑን የሐይማኖት አባቶቹ ያሰምሩበታል። በዚህም በተለይ ህዝቦች ስለ ሰላም ያላቸው አመለካከት በመልካም እንዲቀረጽ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸው የሚያምኑት የሃይማኖት አባቶቹ ስለ ሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። ከሀይማኖት አባቶች መካከልንቡረ እድ ቆሞስ አባ መሃሪ ሀብቴ  "ስለ ሰላም ቅድሚያ ሰጥተን እናስተምራለን ያለ ሰላም ትምህርት የለም የቤተክርስትያን ትምህርት ርእሱ ሰላም ነው ፍቅር አንድነት ነው ይሄ የሌለው ትምህርት የለም እና ሰላምን መሰረት አድርገን እንሰራለን ከዚህ ውጪ ትምህረት የለም፤ ይህች አገር የሰላም አገር ናት አገራችን የእውቀት የፍቅር የአንድነት አገር ናትና አሁን ይሄ ሰላሟ እንዳይደፈርስ እንድትቀጥሉበት ።" ብለዋል፡፡ ሀጂ ኡስማን ኑር የተባሉት አባት "እኛ ስለ ሰላም ሌት ተቀን ሳንል በጣም ይሰበካል በሙስልም ህብረተሰብ ኢስላም ማለት ሰላም ነው በሰላም ምክንያት ሁሉም ህብረተሰብ እንደድሮው በአንድነት አብሮ ታቅፎና ተደጋግፎ እንደሚኖረው አሁንም በዚሁ እንዲቀጥል ሰበካ ይካሄዳል በየቦታው ከድሮ ጀምሮ ኢትዮጵያ አንድ ናት ሙስሊም ክርስቲያን ትልቅ ትንሽ ሳይል በአንድነት አብሮ የሚኖርባት አገር ናት አሁን አንዳንድ ቦታ የሚታየውን ነገር ያሳስበናል ።" ነው ያሉት፡፡ እንደ ሃይማኖት አባቶቹ ገለጻ፤  በአገሪቱ ከሚኖሩ ህዝቦች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዙትና ትልቅ ሃላፊነት የሚጣልባቸው ነገ ተምረው ቤተሰቦቻቸውንና አገራቸውን የሚጠቅሙ ተማሪዎች ናቸው። በመሆኑም በየአካባቢው በየደረጃው ያሉ ተማሪዎች በማይጠቅሙ አሉባልታዎች ሳይታለሉ በአግባቡ ተምረው ትልቅ ቦታ ላይ ለመድረስና በጎ ስራ ለመስራት መትጋት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም