ወጣቶች የህገወጥ አዘዋዋሪዎች ሰለባ እንዳይሆኑ በአገር ውስጥ የስራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል-ዶክተር ማርቆስ

73
አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2011 ወጣቶች የህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ሰለባ እንዳይሆኑ በአገር ውስጥ የስራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ ገለጹ። ዶክተር ማርቆስ በአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የአፍሪካ ቀንድ እና ስደተኞች ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሳይመን ሞርዱ ጋር ተወያዩ፡፡ ዶክተር ማርቆስ በሞሮኮ ማራካሽ እየተካሄደ ባለው የስደተኞች ተሳታፊ ከሆኑት ሳይመን ሞርዱ ጋር ባደረጉት ውይይት ወጣቶች የህገወጥ አዘዋዋሪዎች ሰለባ እንዳይሆኑ በአገር ውስጥ የስራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ እየተወሰደ ያሉ አበይት ፖለቲካዊ እርምጃዎች፤ የተሰሩት አገር የማረጋጋት ስራዎችና በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላም ማውረድ መቻሉ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል፡፡ ዜጎች ከሀገራቸው እንዳይሰደዱ ለመከላከል በሀገር ቤት ኢኮኖሚያዊ እድሎች እንዲፈጠር ትኩረት መሰጠት እንዳለበትም ያስረዱት ዶክተር ማርቆስ ፤ የአውሮፓ ህብረት የስደተኞችን ፍሰት ለመገደብና የመጡት ለውጦችን ለመደገፍ ና ልምዱን ለማከፈል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴንም አድንቀዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተር ሳይመን ሞርዱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና አንድነት በማጠናከር መልካም ጉርብትና እና ግንኙነት በማሳለጥ የኢኮኖሚ አንድነትን በማስተሳሰር የማይተካ ሚና እየተወጣች መሆኑን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም