ዩኒቨርሲቲ - 'ትንሿ' ኢትዮጵያ ማለት ነው

219
አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2011 'ዩኒቨርሲቲዎቻችን የኢትዮጵያዊነት መገለጫ በመሆናቸው ልዩነትን አቻችሎ በአንድነትና በፍቅር የሚኖሩበት ስፍራ ሊሆን ይገባል' ሲሉ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ። በአገሪቱ የሚገኙት ዩኒቨርሰቲዎች የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተወላጆችን፣ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችንና ባህል ባለቤት የሆኑ ወጣቶችን በአንድ ላይ አቅፈው የያዙ በመሆናቸው የኢትዮጵያዊነት ማሳያ መሆናቸውን ነው ተማሪዎቹ የገለፁት። ተቋማቱ በኢትዮጵያዊያን መካከል አንድነትንና መተሳሰብን ለማጠናከር ዓይነተኛ ሥፍራ ተደርገው መወሰድ እንዳለባቸውም አመልክተዋል። በመሆኑም ዩኒቨርሰቲዎችን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች ልዩነቶችን በማቻቻል፤ በመካከላቸው ፍቅርና መተሳሰብን በማጎልበት የዩኒቨርሲቲ ህይወታቸውን የተሳካ ለማደረግ መጣር ይኖርባቸዋልም ብለዋል። ተማሪዎች የብሄር ልዩነትን ከሚያንፀባርቅ አላስፈላጊ አስተሳሰብ ራሳቸውን ማራቅ አለባቸው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ከዚህ ይልቅ የመከባበርና የመተሳሰብ የኢትዮጵያዊያንን የኖረ እሴት በማጠናከር ላይ መትጋት እንደሚገባም መክረዋል። ወጣት ጸጋው ዮሃንስ የ2ኛ አመት የአርት ተማሪ ሲሆን “እያንዳንዱ ብሄር የሚገኙባት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው፡፡ ያንን እንደ አክሱም ዩኒቨርሲቲ ስናየው... እጅግ ሰላም የሰፈነባት የማንኛውም ብሄረሰብ ተማሪዎች ተመሳስለውና አንድ ማህበረሰብ መስለው የሚኖሩበት ቦታ ነው፡፡” ብሏል፡፡ ወጣት ሮቤል አዱኛ ደግሞ 3ኛ አመት የማኔጅመንት ተማሪ ነው"ዩኒቨርሲቲ ማለት ትንሿ ኢትዮጵያ ማለት ነው ከተለያዩ ብሄረሰብ ክፍሎች የሚመጡ የሚጠራቀሙበትና በአንድ ላይ ሆነው የተለያዩ ባህልና ቋንቋ ቢኖራቸውም ያንን አቻችለው የሚሄዱበት ነው፡፡ ለእኔ አክሱም ዩኒቨርሲቲ በጣም የማመሰግነው ነው ሁሉም ሰው የራሱን ይዞ ግን ተቻችለን ነው የምንኖረው ሌላ ቦታ የምንሰማው አይነት ነገር የለም ፍቅርና ሰላም አለ የአካባቢው ማህበረሰብና የጊቢ ተማሪዎች ጥሩ ግንኙነት አላቸው።" ነው ያለው፡፡ የ3ኛ አመት የህግ ተማሪዋ ወጣት ማህሌት ተሻለም የሌሎቹን ሀሳብ ትጋራለች "እኛ በአገራችን ሰላም እንዲሰፍን በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን አስተዋጽኦ ማድረግ ያለብን በሁሉም አካባቢ የሚኖሩ ወላጆችን፣ ወንድሞቻችንን ራሽናሊቲ እንዲኖራቸው ብሄርተኝነት  እንዳይሆኑ ሁሉንም በእኩል የማየት ነገር እንዲኖራቸው እንመክራለን።" ወጣት ፍጹም ህሉፍ በበኩሉ "የብሄር ተኮር ግጭት የሚያነሱ ይኖራሉ ግን ይሄ ራስን ያለማወቅ ነው ወላጅ እንዲማሩ ነው ወደ ትምህርት ቤት የሚልከው እንጂ ግጭት እንዲያነሳ አይደለም ብሏል፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙት ከ40 የሚልቁ ዩኒቨርስቲዎች መካከል አንዳንዶቹ ምክንያቱ በውል በማይታወቅ መንገድ የመማር ማስተማር ሂደት ሲታወክባቸው ይስተዋላል። የአክሱም ዩኒቨርሲቲ በእስከ ዛሬው የመማር ማስተማር ሂደት ተማሪዎች በሰላም ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙበትና ምሳሌ የሆነ ተቋም መሆኑ ይነገራል። ለዚህም የበኩላቸውን ላበረከቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አውቅና የሰጠ መርሃ ግብር ባለፈው ሳምንት በዩኒቨርስቲው ተከናውኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም