ፍርድ ቤቱ በሁለቱ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ፖሊስ የጠየቀውን 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ

67
አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2011 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት አቶ መዓሾ ኪዳኔ ዓለሙ እና አቶ ሀዱሽ ካሳ ደስታ ላይ ፍርድ ቤቱ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቀደ። ዛሬ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው የታየው በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩት አቶ መዓሾ እና አቶ ሀዱሽ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ፖሊስ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ ትናንት ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት በግላቸው ጠበቃ አቁመው ለመከራከር አቅም የሌላቸው መሆኑን ገልጸው መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪዎቹ በቂ ሃብትና ንብረት ያላቸው በመሆኑ በግል ጠበቃ አቁመው መከራከር እንዳለባቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። በመሆኑም ለምርመራ የተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ከመድረሱ በፊት የተጠርጣሪዎቹን ሀብት ንብረት የሚያሳይ ማስረጃ ለታህሳስ 8 ቀን 2011 ዓ.ም ፖሊስ እንዲያቀርብ ታዟል። የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች የነበሩት አቶ መዓሾ እና አቶ ሀዱሽ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም መሆኑ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም