ፍርድ ቤቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል የተጠረጠሩት እነ ጎሃ አጽብሃ ላይ ዋስትና ወይም ጊዜ ቀጠሮ ለመፍቀድ ለነገ ቀጠረ

63
አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2011 በሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀል ተጠርጥረው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው የነበሩ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ወይም ዋስትና ለመፍቀድ ፍርድ ቤት ለነገ ቀጠረ። በጎሃ አጽብሃ መዝገብ የተካተቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀናት ለምርመራ እንዲሰጠው ጠይቋል። ዛሬ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው የታየው ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ ፖሊስ ባለፉት 14 ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት አስረድቷል። የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ደንበኞቻቸው የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፖሊስ በግልጽ እንዳላቀረበ ገልጸዋል። ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ ማስረጃ ለማሰባሰብ የ21 ሰዎችን ምስክርነት መስማቱን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ምስክርነት የሰጡ ሰዎች በነማን ላይ ምስክርነት እንደሰጡ ግልጽ እንዲሆን ጠይቀዋል። ''ደንበኞቻችን የተጠረጠሩበት ነገር በዝርዝር አልተቀመጠም፣ ፖሊስ በቂ ማስረጃ አላቀረበም'' በማለት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፈቀድ እንደሌለበትና ዋስትና እንዲፈቀድ ጠይቀዋል። ደንበኞቻቸው የተጠረጠሩበትን ጉዳይ እንደማያውቁ የገለጹት ጠበቆች ጉዳዩ በተናጠል እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። 'በጅምላ በሰብዓዊ መብት ጥሰት' በሚል መቅረባቸው የፍትህ ስርዓቱን ያዛባል ሲሉ ጠበቆቹ ገልጸዋል። ተጠርጣሪዎች ቃል እንዲሰጡ ሌላ ስልት መጠቀምም ለሰብዓዊ መብት ጥሰት በር የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል። ፖሊስ በእነ ጎሃ አጽብሃ መዝገብ ተጠርጣሪዎች ላይ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመፍቀድ ወይም ለተጠርጣሪዎች ዋስትና ለመፍቀድና የቀሪ ተጠርጣሪዎችን ጠበቆች ለማዳመጥ ፍርድ ቤቱ ለነገ ቀጠሮ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም