በኢትዮጵያ ህገ መንግስትን ጠንቅቆ የመረዳት ችግር በከፍተኛ አመራሩ ጭምር ይስተዋላል- የህግ ምሁራን

154
አዲስ አበባ ታህሳስ 2/2011 በኢትዮጵያ ህገ መንግስትን ጠንቅቆ የመረዳት ችግር ከማህበረሰቡ ባለፈ በከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ላይ እንደሚስተዋል የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ። ህገ መንግስት የዜጎችን መብትና የመንግስትን የስልጣን ገደብ የሚያስቀምጥ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ሲሆን በመንግስትና በዜጎቹ መካከል የተደረገ ቃል ኪዳንም ነው። አንድ ሀገር ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩባት፣ ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና እድገት ያለባት ሆና ለመቀጠል ህገ መንግስት የራሱ ከፍተኛ ሚና እንዳለውም እሙን ነው። ይህንን ጠንቅቆ ያለመረዳትና ህገ መንግስቱን በተሳሳተ መንገድ የመተርጎም ችግር  በአገሪቷ ለተከሰቱ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ተጠቃሽ ነው። ምሁራኑ እንደሚሉት በአገሪቷ በህገ መንግስት ዙሪያ የሚታየው የግንዛቤ ችግር በአፋጣኝ ካልተፈታ የሚወጡ ህጎችና ደንቦች እንዳይከበሩ በር ይከፍታል። የህግ ምሁሩ ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ እንደሚሉት "ህብረተሰቡ፣ የገዥ ፓርቲ አመራሮችና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ህገ መንግስታዊ ግንዛቤያቸው በጣም ደካማ ሲሆን አንዳንድ ጊዜም የተሳሳተ ሆኖ የምናገኝበት ሁኔታ አለ"። በአገሪቷ የህገ መንግስት በአግባቡ ተረድቶ የመተግበር ችግር፣ ህገ መንግስቱ ለራስ ዓላማ ማራመጃነት የመጠቀም አዝማሚያና ህዝቡ በህገ መንግስቱ ላይ ያለው አመኔታ የማጣት ችግሮች ሰፊ ናቸው። በህገ መንግስት ውስጥ ያሉ መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች በአግባቡ አለመረዳትም ህግችና አዋጆች እንዲሸራረፉና እንዲጣሱ ከማድረጉም ባለፈ ህዝቡም በህገ መንግስት ላይ እምነት  እንዳይኖረው አድርጓል። የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ካየን ህገ- መንግስትን በአግባቡ ካለመረዳት የተነሳ በህገ መንግስት ውስጥ ያሉ መልካም ነገሮችን በደንብ ያለማየትና ያለመገንዘብ ህዝቡም እንዲያውቃቸውና እንዲገነዘብ ያለማድረግ ከዚያ ይልቅ ችግር አላባቸው ብለው የሚያስቧቸውን  አንድ ወይም ሁለት አርቲክሎችንና ድንጋጌዎችን አጉልተው ማሳየት ይቀናቸዋል። መንግስት ከከፍተኛ አመራሮቹ ጀምሮ የህገ መንግስቱን ዝርዝር ድንጋጌዎች የማሳወቅና በአግባቡ እንዲተገበርም የማድረግ ስራ መስራት አለበት ይላሉ ምሁራኑ። ህገ መንግስቱ በርካታ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ድንጋጌዎችን የያዘና ሰፊ በመሆኑ ይህንን ተረድቶ የሚያስፈጽም የእኔ ነው የሚል ትውልድ መፈጠር እንዳለበትም ተናግረዋል ዶክተር ሲሳይ ። ይህ ህገ መንግስት ብዙ ጠቃሚ ነገሮች ብዙ የሚያስማሙ ነገሮች እንዳሉት መታመን አለበትያሉት ምሁሩ ከህገ መንግስት አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ከአንቀጽ 13 እስከ 42 የሚሆነው ሰብዓዊ መብቶችና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአጠቃላይ መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች በሚል ርዕስ ያካተተ ነው ብለዋል። ሌላኛው የህግ ባለሙያ አቶ አማን ኡመር "በአገሪቷ የህገ መንግስት አረዳድ ችግር አለ፤ ህገ መንግስቱን አውቀናል የሚሉትም በተሳሳተ መልኩ የመተርጎም ችግር አለባቸው" ይላሉ። በክልልና በፌዴራል መንግስት የሚነሱ አንዳንድ እሰጥ አገባዎች በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጡ ድንጋጌዎች በአግባቡ ያለመተግበር ማሳያዎች ናቸው ብለዋል። በተለይ የክልል የአመራር አካላት ህገ መንግስቱን በአግባቡ አውቀው ማሳወቅና ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ለህብረተሰቡ ፈጣን ምላሽ መስጠት ይገባቸዋል ነገር ግን ፈጣን ምላሽ በማይሰጣቸው ጉዳዮች ህብረተሰቡ መብቱን ለማስከበርና ምላሽ ለማግኘት ሃይልን ይጠቀማል፤ ይህ ደግሞ አካባቢን ለአላስፈላጊ ችግር ይዳርጋል ብለዋል። ''አንድን ክልል የሚመራ የክልል አስተዳደር ህዝቡ አስቀድሞ ህገ መንግስትንና የአሰራር ስርዓቱን የሚነሱ ጥያቄዎች ክልል በሚችለው መልኩ ምላሽ መስጠት ከሱ አቅም በላይ የሆነው ለፌዴራል መንግስት የማቅረብ ስራ ካልሰራ ህዝቡ ከሱ አስቀድሞ የሚረዳ ከሆነ ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ በራሱ ሃይል የሚራመድ ከሆነ ችግሮች መፈጠራቸው አይቀረም።” ነው ሉት፡፡ ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታትና በህዝብና በመንግስት መካከልያለውን የመተማማን መንፈስ አሳድጎ ፍትህ የሰፈነባት አገር ለመገንባት ህገ መንግስት ላይ ያለውን የግንዛቤ ችግር መፍታት ያስፈልጋልም ብለዋል። ህገ መንግስት የአንድ ሀገር የበላይ ህግ የሆነና የሀገሪቷ ዜጎች አብረው በጋራ ለመኖርና ለማደግ እንመራበታለን በማለት የተስማሙበት ሰነድ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም