ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ቡድን ለካንሰር ማእከል የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

71
አዲስ አበባ ህዳር 1/2011 እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን በመደገፍ የመረዳዳት ባህላችንን ማጠናከር ይገባናል ሲሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ገለጹ። ክለቡ 83ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በ'ተስፋ አዲስ ፓረንትስ ቻይልድ ሁድ ካንሰር ማዕከል' የሚገኙ ታማሚ ህጻናትን በመጎብኘትና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ድጋፍ በማድረግ አክብሯል። በአሁኑ ወቅት በካንሰር ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከሉ ከ5 ወር ጀምሮ እስከ 16 ዓመት የሚሆኑ ታማሚ ህጻናት ይገኛሉ። በዚህም ከክለቡ  ደጋፊዎች በተሰበሰበ ከ30 ሺህ ብር በላይ ለታማሚ ህጻናት ምግብና መጠጦችን፣ የንጽህና መጠበቂያዎች፣ የትምህርት መሳሪያዎችና ሌሎችም አስፈላጊ ግብዓቶችን ድጋፍ አድርገዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የክለቡ ደጋፊዎችም በዚህ በጎ ተግባር ላይ በመሳተፋቸው ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል። በየአካባቢው ብዙ ችግር ያለባቸውና እርዳታ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች በርካታ በመሆናቸው ሁሉም ከየአካባቢው ከጎረቤቱ ጀምሮ የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህልን ማጎልበት ይገባል ብለዋል። የማህበረሰባዊ ተሳትፎን በማጎልበት የኢትዮጵያዊነት ባህልንና በጋራ የመኖር እሴቶችን ጠብቆ የተሻለች አገርና ዜጋን መፍጠር አለብን ሲሉም ተናግረዋል። በልገሳው ላይ የተሳተፈቺው የክለቡ ደጋፊ ወጣት እሌኒ ተስፋዬ እንዳለችው˝ልጆቹ  በቀን አንድ እንቁላልና ወተት ግዴታ ያስፈልጋቸዋል። ይሄንን ለማድረግ ደግሞ አቅሙ አይፈቅድላቸውም፤ ስለዚህ  ሁላችንም የበኩላችንን ማድረግ አለብን ህጻናቶች ነገ የአገር ተረካቢዎች ናቸው።˝ ˝በአብዛኛው  በልግስ  የሚሰጡ ነገሮች  የሰውን አእምሮ ቀስቅሰውና ማህበረሰባዊ ተሳትፎን የተሻለ መረዳዳትን እንዲያጎለብት ነው ፤ እንጂ በስጦታ የሚደረግ ነገር በቂ ነው ማለት አይደለም እና ሌሎችም ማህበረሰቦች ብዙ ነገር የጎደላቸው አሉ ከአካባቢያችን ከጎረቤቶቻችን ጀምረን በመተሳሰብ ኢትዮጵያዊነት ባህላችንን ጠብቀን የተሻለ ሀገርና  ዜጋ  መፍጠር እንችላለን ብዬ አስባለው ˝ በማለት የገለጸችው የቡድኑ ደጋፊ ወጣት ለአለም አሱኔ ነች፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ባለፉት 83 ዓመታት ታሪኩ የበርካታ ድሎች ባለቤት ብቻ ሳይሆን "የበጎ ተግባር ተምሳሌትም ጭምር ነው" ያሉት ደጋፊዎቹ በቀጣይ በእንደነዚህ አይነት በጎ ተግባር ላይ በመሳተፍ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ  የስፖርት ማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ምኒሊክ ግርማ በበኩሉ ክለቡ የምስረታ በዓሉን በተለያዩ በጎ አድራጎት ፕሮግራሞች ማካሄዱን የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው፤ አሁን የተደረገው በጎ ተግባር በቂ ሆኖ ሳይሆን በጎ ተግባርን ለማበረታታት የተደረገ ነው ብለዋል። ህክምናው  ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅና ለታካሚዎች አቅምም ከባድ በመሆኑ መንግስትና የተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል ያሉት ደግሞ የማዕከሉ ተወካይ ወይዘሮ ፍሬወይኒ ገብረመድህን ናቸው። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ዳንኤል ገብረሚካኤል በበኩላቸው ሚኒስቴሩ በተለይ የካንሰር ህክምና ሳይቆራረጥ እንዲሰጥ ድጋፍ ሰጪ ተቋማትን የመደገፍና የህክምና ማዕከላትንም ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የስፖርት ማህበሩ በቀጣይም የክለቡን 83ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን አስመልክቶ ባዛርና ኤግዚቢሽኖችን የማካሄድ እንዲሁም የደም ልገሳና ሌሎች የበጎ አድራጎት መርሃ ግብሮችን እንደሚያካሄድም ተናግረዋል። ከዚህም መካከል በመጪው ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም ከሁለት ሺህ በላይ የክለቡ ደጋፊዎችን የሚያሳትፍ የደም ልገሳ መርሃ ግብር እንደሚያካሄድ ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም