በጋምቤላ ክልል የማህጸን በር ካንሳር መከላከያ ክትባት ተጀመረ

139
ጋምቤላ ታህሳስ 1/2011 በጋምቤላ ክልል የማህጸን በር ካንሳር ለመከላከል ዕድሜቸው 14 ዓመት ለሆናቸው ልጃገረዶች ክትባት መሰጠት ተጀመር። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡማድ ኡጁሉ ክትባቱን ዛሬ  ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለጹት መንግስት የተለያዩ የክትባት መረሃ ግብሮችን በማጠናከር የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል ። ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት ስራዎች በዘርፍ ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው በቀጣይም እናቶችንና ህጻናትን ከበሽታ ጉዳት ለመታደግ  በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ እቅዶች ተነድፋው ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት እየተሰጠ ያለው የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት የዚሁ አካል መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል። በዕለቱ ለተጀመረው የክትባት  መረሃ ግብር ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኡማን አሙሉ በበኩላቸው " የማህጸን በር ካንሳር በሽታ በተለይም በሴቶች ላይ ከፍተኛ የህመምና የሞት ጉዳት እያደረሰ ነው "ብለዋል። መንግስት የመከላከያ ክትባት ለታዳጊዎች በመስጠት በሽታውን አስቀድሞ ለመከላከልና የተጠቁትንም የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ  14 ዓመት ለሆናቸው ልጃ ገረዶች   በትምህርት ቤቶችና በየቀበሌው ክትባቱን የመስጠት ስራ መጀመሩን አስታቀዋል። ኃላፊው እንዳሉት ከታሳስ 1 ቀን 2011 ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሚቆየው ክትባት ሰባት ሺህ የሚሆኑ ልጃ ገረዶችን በክትባቱ ሽፋን ለመስጠት ታቅዷል። በክልሉ ዕድሜቸው ከዘጠኝ ዓመት ጀምሮ ለሚገኙ ልጃ ገረዶች ክትባቱን ለመስጠት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በአቅም ውስንነት ምክንያት ለጊዜው  14 ዓመት ለሆናቸው ብቻ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በቢሮው የጤና ማበልጸግና የበሽታ መከላከል የስራ ሂደት ኃላፊ አቶ ሪያንግ ፖች ናቸው፡፡ በቀጣይ  ከዘጠኝ ዓመት ጀምሮ ለሚገኙ ልጃ ገረዶች ክትባቱን ለመስጠት ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም