የኦዲት ግኝቶች ሪፖርቶች ቢቀርቡም ተጠያቂነትን ማስፈን አልተቻለም--የክልሎች ዋና ኦዲተሮች

64
አዲስ አበባ ታህሳስ 1/2011 የኦዲት ግኝቶችን በተመለከተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች በየጊዜው ሪፖርተቶች ቢቀርቡም የተጠያቂነት ሥርዓት ማስፈን እንዳልተቻለ የተለያዩ ክልሎች ዋና ኦዲተሮች ተናገሩ። የጋምቤላ ክልል ምክትል ዋና ኦዲተር ኡኩዲ ኡቦያ እንዳሉት፤ በግንባታ ጥራት፣ በሰነድና በገንዘብ ጉድለት እንዲሁም በገቢ አሰባሰብ ላይ ተደጋጋሚ የኦዲት ክፍተቶች ተገኝተዋል። በክልሉ በተደጋጋሚ የኦዲት ክፍተት ከሚታይባቸው ተቋማት ውስጥ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አንዱ መሆኑን ገልጸው ተቋሙ ባለፈው በጀት ዓመት ከ667 ሺህ ብር በላይ በግለሰቦች የተመዘበረ መሆኑን በኦዲት መረጋገጡን ተናግረዋል። ''ይህን የኦዲት ክፍተት ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቀን ብሩ እንዲመለስ ብንጠይቅም ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደም'' ብለዋል። የደቡብ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ዋና ኦዲተር አቶ ተስፋዬ ታፈሰ በበኩላቸው በክልሉ በተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት የሚታይባቸው የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ዘርፎች መሆናቸውን ገልጸዋል። ተቋማቱ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ የማይወሰድባቸው በመሆኑ ካለባቸው ችግር ከመውጣት ይልቅ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን አስረድተዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ የክልል ምክር ቤቶች የኦዲት ግኝትን ተከትሎ የተጠያቂነት አሰራርን ለማስፈን የሚወስዱት እርምጃ እንደሌለ ገልጸዋል። የአማራ ክልል ዋና ኦዲተር አቶ ገረመው ወርቁ በበኩላቸው በክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች ተደጋጋሚ የኦዲት ጉድለቶች እንደሚታይባቸው ተናግረዋል። በምዕራብ ጎጃም ጎንጂ ቆለላ ወረዳ ለአርሶ አደሮች በዕርዳታ የሚሰራጭ ምርጥ ዘር አርሶ አደሮች እንደወሰዱ በማስመሰል ምዝበራ መካሄዱን በኦዲት ግኝት መረጋገጡን ገልጸዋል። በክልሉ በሚደረጉ የኦዲት ግኝቶች ላይ የሚመለከታቸው አካላት አጥጋቢ እርምጃ እየወሰዱ አለመሆናቸውንም ዋና ኦዲተሩ ተናግረዋል። የከፋ የኦዲት ችግር ላለባቸው ተቋማት ስልጠና በመስጠት ችግሩን እንዲያስተካክሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል። የህዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች እንዲሁም አስፈጻሚው አካል ለኦዲት ግኝቶች ትኩረት በመስጠት የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲዘረጋ ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ወይዘሮ ጽጌወይን ካሳ በበኩላቸው በከተማዋ ከፍተኛ በጀት የሚመደብላቸው ተቋማት ከደንብና መመሪያ ውጪ ግዢ እንደሚፈጽሙ በኦዲት መረጋገጡን ተናግረዋል። የከተማዋ ምክር ቤት የኦዲት ግኝቱን መነሻ በማድረግ ተደጋጋሚ የኦዲት ክፍተት ባለባቸው ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ገልጸዋል። በተከፋይና በተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ የሚስተዋሉ ጉድለቶች እንዲሁም የተቋማት የንብረት አያያዝም ከፍተኛ ችግር እንዳለ በኦዲት ተረጋግጧል ብለዋል። ከ2002 እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ በተደረገ ኦዲት ክፍተት ያለባቸው ተቋማትን በመለየትና በመከታተል 400 ሚሊዮን ብር ተመላሽ መደረጉን ገልጸዋል። የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ላክዴር ላክባክ እንዳሉት፤ የኦዲት ክፍተቱን በአግባቡ በማጣራት በህግ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ተቋማት ላይ እርምጃ ለመውሰድ ምክር ቤቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ክትትል ማድረግ ጀምሯል። ምክር ቤቱ ከሚያደርገው ክትትል ውጭ በተደጋጋሚ የኦዲት ክፍተት የሚያሳዩ ተቋማት ክፍተቱን እንዲያስተካክሉ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ባለፈ እስከ አሁን ህጋዊ እርምጃ አለመውሰዱን አፈ ጉባዔው አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም