8ኛው የአካል ጉዳተኞችና መስማት የተሳናቸው የስፖርት ፌስቲቫል ፍጻሜውን አገኘ

77
አዲስ አበባ ታህሳስ 1/2011 ለ8ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የአካል ጉዳተኞችና መስማት የተሳናቸው የስፖርት ፌስቲቫል በዛሬው እለት ፍጻሜውን አገኘ። ፌስቲቫሉ በአዲስ አበባ ከተማ ስፖርትና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በትብብር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አዘጋጅነት ነው ላለፉት 10 ቀናት የተካሄደው። በዛሬው የመዝጊያ ዝግጅትም የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ቢሮ ኃላፊን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በድምቀት ተጠናቋል። ውድድሩ በአራት ዘመናዊ የስፖርት አይነቶችና በሶስት የፊስቲቫል ስፖርቶች መካከል ነው ሲካሄድ የቆየው። በዛሬው የፍጻሜው እለትም በእግር ጉዳት የወንዶች ገመድ ጉተታ ውድድር በልደታና ኮልፌ ቀራኒዮ  ክፍለ ከተማ መካከል የተደረገ ሲሆን ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል። በዚህ ውድድር መስማት በተሳናቸው ስፖርቶች መካከል የተደረገውን ፉክክር በአጠቃላይ የካ ክፍለ ከተማ አሸናፊ መሆን ችሏል። በፓራሊምፒክ ስፖርቶች ልደታ ክፍለ ከተማ የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል። በዚህ ውድድር ላይ  የፀባይ ዋንጫውን ደግሞ የካ ክፍለ ከተማ አሸናፊ በመሆኑ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል። ይህ ውድድርና ፌስቲቫሉ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን በመጪው ዓመት ለ9ኛ ጊዜ በልደታ ክፍለ ከተማ አዘጋጅነት የሚደረግ ይሆናል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም