በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች በግብአት እጥረት ሳቢያ ሥራቸውን ማካሄድ እንዳልቻሉ ገለፁ

162
አዲስ አበባ ታህሳስ 1/2011 አዲስ አበባ ውስጥ በአነስተኛና ጥቃቅን የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች በግብአት እጥረት ሳቢያ ሥራቸውን በተገቢው መንገድ ማካሄድ እንዳልቻሉ ገለፁ። በዚህም የተነሳ በብድር ያገኟቸው የተለያዩ ማሽኖች ያለስራ ተቀምጠዋል፤ ይህም ለኪሳራ እየዳረጋቸው እንደሆነ አክለዋል። አዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስና ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበር በበኩሉ የግብአት እጥረት ችግሩን ለመቀነስ ማሽኖቹን በብድር ማቅረቡን አስታውቋል። ከሁለት ዓመት በፊት በሶሰት አባላት የተመሰረተው "ሮዛ ብርሃኑና ጓደኞቻቸው ልብስ ስፌት የህብረት ሽርክና ማህበር"   መስራች ወይዘሮ ሮዛ ወልደአምላክ በብድር በተገኙ ዘጠኝ ማሽኖች ስራ የጀመረው ድርጅታቸው በጨርቅ እጥረት ሳቢያ የሚጠበቅበትን ምርት ማቅረብ ተስኖታል ይላሉ። በአሁኑ ወቀት 28 ሰራተኞችን የሥራ ባለቤት ያደረገው ድርጅቱ እንዲጠናከር ያለምንም መያዣ መንግሰት እያደረገ ያለው ድጋፍ ግን በእጅጉ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል። ከአዲስ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስና ንግድ ስራ በብደር በተገኙ 19 ማሽኖች በ2007 ዓ.ም ሥራውን የጀመረው ሰለሞን የጣሳና ቆርኪ ፋብሪካ ተመሳሳይ ችግር ገጥሞታል። የድርጅቱ መስራች አቶ ሰለሞን መንበረ እንደሚሉት በቆርቆሮና ብረታብረት ጥሬ እቃ እጥረት ምክንያት ድርጅቱ ከገዢዎች ጋር የገባውን ውል እንኳ በወጉ መፈፀም እንደተሳነው ገልፀዋል። ድርጅቱ ለደንበኛው ለማቅረበ ከገባው የምርት ውል ማሳካት የቻለው ግማሽ ያህሉን ብቻ መሆኑን አንስተዋል። ማሽኖቹ ያለ ሥራ በመቀመጣቸውም ሰራተኞች ያለስራ ጊዜያቸውን እንዲያጠፉ፤ ድርጅቱም የወር ደምወዝ በመክፈል ለኪሳራ እንዲዳደረግ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል። "ድርጅቱ በየአመቱ ማስፋፊያ በማድረግ የሰራተኛንና የማሽን ቁጥር የማሳደግ እቅድ የያዘ ቢሆንም የጥሬ እቃ አቅርቦቱ ግን ይህንን እንዳያሳካ እንቅፋት ሆኖበታል" ሲሊም ተናግረዋል። በመሆኑም ማሽኖቹን በብድር የሚያቀርበው አዲስ ካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ችግሩ የሚፈታበትን መንገድ እንዲዘይዱ የማህበራቱ መስራቾች ጠይቀዋል። የአዲስ ካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበር ችግሩን ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰራ የማህበሩ የፕሮሞሽን ባለሙያ አቶ ፀጋዬ ሽንብር ለኢዜአ ገልፀዋል። ማህበሩ ብቻውን ለውጥ ማምጣት ስለማይችል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የጋራ እቅድ መታቀዱን ጠቅሰው እየገጠሙ ያሉ የግብዓትና ሌሎች ችግሮች በዚህ ሂደት እንደሚፈቱም ነው ያብራሩት።  የማህበሩን ተልዕኮ ለማሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካል እንዲረባረብም አቶ ፀጋዬ ጥሪ አቅርበዋል። አዲስ ካፒታል እቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበር በ2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በከተማዋ የልማት ተቋማት የተቋቋመ የልማት ድርጅት ነው። ማህበሩ በዋናነት በአምራች ዘርፍ ለተሰማሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የማምረቻ መሳሪያዎችን ገዝቶ በማቅረብ የመሳሪያ ሊዝ አገልግሎት ይሰጣል። ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ  ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ 4 ሺህ 653 የካፒታል እቃዎችን ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል። በዚህም 2 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ ሆነዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም 250 ሚሊዮን ብድር በመመደብ 2 ሺህ 500 ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም