ለጋምቤላ ክልል የእርሻ መሬት ተስማሚ የማዳበሪያ ዓይነት በጥናት ተለየ

70
ጋምቤላ ታህሳስ 1/2011 ለጋምቤላ ክልል የእርሻ መሬት ተስማሚ  የማዳበሪያ ዓይነት በጥናት መለየቱን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው በክልሉ ሲካሄድ የቆየውን የአፈር ለምነትና የማዳበሪያ አጠቃቀም ምክር ሃሳብ ጥናት አጠናቆ ይፋ አድርጓል። ጥናቱ ይፋ በተደረገበት ስነስርዓት ወቅት በኤጀንሲው የአፈር መረጃ ስርዓት ፕሮጀክት ቡድን መሪ አቶ ተግባሩ በለጠ ንደተናገሩት ክልሉ ከሌሎች አካባቢ የተሻለ የደን ሽፋን ያለበትና ብዙ የእርሻ ስራ ያልተስፋፋበት አካባቢ ነው። የክልሉ የእርሻ መሬት የአፈር ባህሪ ሁሉም ሊባል በሚችል መልኩ አሲዳማ  ቢሆንም አፈሩ ለእርሻ ስራ ችግር የማይፈጥር እንደሆነ በጥናቱ መለየቱን ገልጸዋል። በክልሉ ያለው የእርሻ መሬት ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ ፎስፎርስ የተባለው ንጥር ነገር በስፋት ያለበት አካባቢ መሆኑን ጠቁመው በአንፃሩ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የ "ቦሮን"  ንጥር ነገር እጥረት እንዳለ በጥናቱ መረጋገጡን አስረድተዋል። በዚህ ምክንያት ለክልሉ የእርሻ መሬት ስምንት የማዳበሪያ ዓይነት እንደሚያስፈልግ በጥናት መለየቱን ቡድን መሪው ተናግረዋል፡፡ በጥናቱ ለክልሉ የእርሻ መሬት እንደሚያስፈልጉ ከተለዩት የማዳበሪያ ዓይነቶች መካከል ዩሪያ ፣ፓታሽ፣ ቦሮን እና ፎስፌት የተባሉት እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡ እንደ ቡድን መሪው ገለፃ ጥናቱን የክልሉ  አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ማድረግ ያስፈለገው  ተጨማሪ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ያለመ ነው። የክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ በበኩላቸው በክልሉ በተለምዶ መሬቱ ለምና ድንግል ነው በሚል አስተሳሰብ አርሶ አደሩ እስካሁን የኬሚካል ማዳበሪያዎችን ሳይጠቀም መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት አርሶ አደሩ በሄክታር የሚያገኘው ምርት ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ጋር ሲነፃፀር በሶስት እጥፍ ዝቅ ያለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የቢሮው  ኃላፊ እንዳሉት አርሶ አደሩ የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ትርፍ አምራች ሳይሆን ለዘመናት ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ሲገፋ  ቆይቷል። በጥናቱ መሰረት ከመጪው የመኸር እርሻ ወቅት ጀምሮ አርሶ አደሮች የሚፈልጉትን የማዳበሪያ ዓይነቶች እንዲጠቀሙ በማድረግ ምርታማነቱን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ጥናቱ ይፋ በተደረገበት ስነስርዓት ወቅት የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ " በክልሉ የተካሄደውን የአፈር ለምነትና ማደበሪያ አጠቃቀም ምክረ ሃሳብ ጥናት ወደ ተግባር በመለወጥ የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ በትኩረት ሊሰራ ይገባል" ብለዋል። በተለይም የጥናቱን ውጤት ወደ ተግባር ለመለወጥ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። የክልሉ የአፈር ለምነትና የማዳበሪያ አጠቃቀም ምክር ሀሳብ ጥናት ካርታ በቅርቡ  ታትሞ ስራ ላይ ይውላል ተብሏል።                              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም