መንግስትና በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ለኦዲት መስሪያ ቤቶች ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ

119
አዲስ አበባ ታህሳስ 01/2011 የኦዲት መስሪያ ቤቶች ነጻና ገለልተኛ ሆነው በህግ የተሰጣቸው ሃላፊነት በብቃት እንዲወጡ መንግስትና በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት እንዲሰጧቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። 20ኛው የፌዴራልና የክልል ዋና ኦዲተሮች ዓመታዊ የጋራ የምክክር ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። በጉባዔው መክፈቻ ምክትል አፈጉባዔ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ እንዳሉት፤ ግልጽ አሰራርና ተጠያቂነትን ለማስፈን የፌዴራልና የክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች የሚያመነጯቸው የኦዲት ግኝቶች የጎላ አስተዋጽኦ አላቸው። በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች የተለያዩ ህጎችን ከማውጣት ባለፈ ለልማት በጀት እንዲመደብና በጀቱ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን የሚከታተሉ መሆኑን ገልጸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተሰጣቸውን ተግባር በአግባቡ እየተወጡ መሆን አለመሆኑን የመቆጣጠርና የመከላከል ብሎም የመደገፍ ሃላፊነት እንደተጣለባቸው ጠቁመዋል። የልማት ስራዎች አፈጻጸም፣ የበጀትና የመንግስት ንብረት አጠቃቀምን የተመለከቱ የኦዲት ሪፖርቶች በየደረጃው ላሉ ምክር ቤቶች ለቁጥጥርና ለክትትል ተግባራት ቁልፍ መሳሪያዎች መሆናቸውንም ወይዘሮ ሽታዬ ገልጸዋል። የኦዲተር መስሪያ ቤቶች የህግ ማዕቀፋቸው ተፈትሾ አስተዳደራዊና የፋይናንስ ነጻነታቸው ጭምር በአግባቡ ተጠንቶ አስፈላጊና ተገቢ የሆኑ ማሻሻያዎችን መውሰድ ተገቢነት እንዳለው አስገንዝበዋል። በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ከዋና ኦዲተር የሚቀርቡ የህዝብና የመንግስት ሃብትና ንብረት በአግባቡ እንዲጠበቅና ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ህዝቦቿ የሚመኙትን ዘላቂ፣ ፍትሃዊና ፈጣን ዕድገት ለማምጣት የአገሪቷ ሃብቶች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ መዋል አለመዋላቸውን ዘወትር መከታተልና መቆጣጠር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል። የፌዴራልና የክልል ኦዲተር መስሪያ ቤቶች አገራዊ የኦዲት ስራ እንዲጎለብትና የተጠያቂነት ስርዓት እንዲጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ከጀመሩ ሁለት አስርት ዓመታትን ማስቆጠራቸውንም አስታውሰዋል። የምክክር መድረኩ ''የዋና ኦዲተር ተቋማት አቅም የሚገነባበት ተሰሚነትና በጎ ፈጣሪነታችንን የምናሳድግበት በጥቅሉም በአገራችን የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ሂደት ውስጥ የተጣለብንን ሃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለንን ስልት የምንቀይስበት ነው" ብለዋል። የኦዲት ስራ ወጥነት ባለው መልኩ በአይነቱ፣ በሽፋኑና በጥራቱ አድጎ በአግባቡ እንዲከወን የኦዲት ግኝቶችም በህግ አውጭው፣ ህግ አስፈጻሚው፣ በህብረተሰቡና በብዙሃን መገናኛ ዘንድ ዋጋ ተሰጥቷቸው የእርምጃ አወሳሰዱ እንዲጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ ዋና ኦዲተሩ አሳስበዋል። በመድረኩ በፌዴራልና በክልል ያሉ ዋና ኦዲተሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሞክሮ የሚለዋወጡበትና ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማምጣት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ምክክር የሚደረግበት መሆኑም ተገልጿል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም