በቡራዩና አካባቢው ግጭት ተጠርጣሪዎች ላይ የግድያ ወንጀል ክስ ሊመሰረት ነው

59
አዲስ አበባ ታህሳስ 1/2011 በቡራዩና አካባቢው ተከስተው የነበሩ ግጭቶች የሽብር ወንጀል ተጠርጣሪዎች ላይ የግድያ ወንጀል ክስ ሊመሰረት ነው። በአብረሃም ተረፈ በሞቲ ደሬሳ መዝገቦች የተጠረጠሩ 17 ግለሰቦች በከፍተኛው ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው ሰታይ ቆይቷል። አቃቤ ህግ ባለፈው ቀጠሮ ክስ መስርቶ እንዲቀርብ በታዘዘው መሰረት ተጠርጣሪዎቹ ዛሬ አራተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል። ይሁንና ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል የምርመራ መዝገብ በቂ ባለመሆኑ በግድያ ወንጀል ክስ እንዲመሰረትባቸው ተወስኗል። በዚሁ መሰረት በአብረሃም ተረፈ መዝገብ የተካተቱ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት በመዝገብ ቁጥር 227015 የሚታይ ይሆናል። በአቶ ሞቲ ደሬሳ መዝገብ በችሎቱ ያልቀረቡ ሁለት ሰዎችን ጨምሮ ሰባት ግለሰቦች ጉዳይም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 20ኛ ወንጀል ችሎት ይታያል። በከፍተኛው ፍርድ ቤት አራተኛ ወንጀል ችሎት የዛሬ ውሎ ሲታይ የነበረው የተጠርጣሪዎቹ መዝገብ ተዘግቶ በ3ኛና በ20ኛ የወንጀል ችሎት በግድያ ወንጀል የክስ ሂደታቸውን እንዲከታተሉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም