በአዋሳኝ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ችግር በባህላዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

118
ዲላ ሚያዝያ 24/2010 በጌዴኦ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ችግር በባህላዊ መንገድ ዘለቄታዊ እልባት እንዲያገኝ በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ የሁለቱ ዞኖች የፀጥታና አስተዳደር አካላት ገለጹ፡፡ ችግሩ በባህላዊ ስርዓት የሚፈታበትን አቅጣጫ ለማስቀመጥ የጌዴኦና የጉጂ ኦሮሞ አባገዳዎች የፀጥታ አካላት በተገኙበት ትናንት በጋራ ተወያይተዋል ፡፡ በውይይቱ ወቅት  የጌዴኦ ዞን ፀጥታና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ እንግዳወርቅ ዳካ እንዳሉት በሁለቱም ዞኖች አዋሳኝ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው አለመግባባት ችግር ምክንያት  ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ፡፡ በሁለቱም ክልሎች የፀጥታና አመራር አካላት እየተደረገ ባለው ጥረትም አካባቢው ተረጋግቶ ነዋሪዎች ወደቀያቸው መመለስ መጀመራቸውን ገልጸዋል ፡፡ እንደ አቶ እንግዳወርቅ ገለፃ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት ባይኖርም ጥቂት ግለሰቦችና አመራሮች በፈጠሩት አሉባልታ ምክንያት አለመግባባት ተፈጥሯል ፡፡ ይህን አለመግባባት ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና ሁለቱም ህዝቦች ወደቀድሞ ወንድማማችነትና አንድነት እንዲመለሱ ለማድረግ ደግሞ በአባገዳዎች አማካይነት በባህላዊ የዕርቅ ስነ-ስርዓት ጥረት እየተደረገ ነው ፡፡ የጌዴኦና የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎች ተቀራርበው እንዲወያዩና ባህላዊ የዕርቅ ስርዓቱን እንዲያከናውኑ ለማመቻቸት ከምዕራብ ጉጂ ዞን የፀጥታና አስተዳደር  አካላት ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ የምዕራብ ጉጂ ዞን ፀጥታና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደለ ወሬራ ችግሩ ተፈጥሮ በነበረበት  ወቅት በጌዴኦ በኩል ብዛት ያላቸው ሰዎች ከምዕራብ ጉጂ ዞን ቢፈናቀሉም በጉጂ ኦሮሞ ቤት ውስጥ ተጠልለው እንክብካቤ ሲደረግላቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ " ይህም በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት አለመኖሩን የሚያሳይ ነው "ብለዋል ፡፡ በህዝቡ መካከል በተነዛው የፀረ ሠላም አጀንዳ በመመራት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ካደረሱ ግለሰቦች መካከል በቁጥጥር ስር የዋሉ እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ ከፌዴራልና ከሁለቱም ክልሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ቀሪዎቹን ለመያዝ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በመንግስት በኩል እየተደረገ ካለው ጥረት በተጓዳኝ በባህላዊ ስርዓት  ዕርቅ ማውረዱ ጉልህ ሚና እንዳለው የገለፁት አቶ ታደለ ይህን ከግብ ለማድረስ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል ፡፡ የጉጂ ኦሮሞ አባገዳ ጂሎ ማኖ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ጌዴኦና ጉጂ ከጥንት ጀምሮ አንድ ሆነው የኖሩ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው ፡፡ በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት ሽረው ወደ ቀድሞ ፍቅራቸው እንዲመለሱም በባህላቸው መሰረት ዕርቅ መፈፀም እንደሚገባ ነው ያመለከቱት፡፡ የጌዴኦ አባ ገዳ ደንቦቢ ማሮ በበኩላቸው "የሚወሩ አሉባልታዎችን ለማስወገድና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የተሳሳቱን ሰዎች  ማስተማርና መምከር ይገባናል "ብለዋል ፡፡ በውይይቱ መጨረሻም በሁለቱ ህዝቦች መካከል በባህላዊ ስርዓት  መሰረት ዕርቅ ለማውረድ ለሚያዚያ 25/2010ዓ.ም. ቀጠሮ ተይዟል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም