የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲጎለብት ይሰራል - አዴፓ

92
አዲስ አበባ ህዳር 30/2011 የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጎለብት እንደሚሰራ አስታወቀ። ፓርቲው የተመሰረተበትን 38ኛ ዓመት ክብረ በዓል "ለውጡን እንደ ንስር ታድሰን እናስቀጥላለን" በሚል መሪ ኃሳብ በአዲስ አበባ እያከበረ ነው። በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊና የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ''ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ለኢትዮጵያዊያን መታገያ መስመር ነበር'' ብለዋል። ፓርቲው ይህንን መስመር በመከተልም ከቀድሞ ኢህዴን ከዛም ወደ ብአዴን አሁን ደግሞ ወደ አዴፓ ወቅታዊ ሁኔታውን ከግምት በማስገባት ሽግግር ማድረጉን አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ በሚታየው ለውጥ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸው ''ለውጡ የአገሪቱን መጻኢ እድል የመወሰን አቅም ስላለው በጥንቃቄ እናስቀጥላለን'' ነው ያሉት። አዴፓ ባለፉት ዓመታት በርካታ ውጣ ውረዶች እንደገጠሙት ገልጸዋል። በቀጣይም ከፍተኛ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ትንበያቸውን አስቀምጠው ፓርቲው ችግሮችን ለመፍታት ከምንግዜውም በላይ እንደሚሰራ ገልጸዋል። በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የሚነሱ በተለየ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ እኩልነት፣ ነጻነትና ሌሎች የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ለመፍታት ፓርቲው እንደሚሰራም አረጋገጠዋል። የወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን በህጋዊ መንገድ ለመፍታተ ፓርቲው እንደሚሰራ ጠቁመው ሌሎች ከሕግ ውጭ የሆኑ አሰራሮችንም ለመታገል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል። ፓርቲው እየሰራቸው ላሉ ሥራዎች የፓርቲው አባላትና መላው የአማራ ሕዝብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም