የአዲስ አበባ መንገዶች በወር አንድ ጊዜ የእግር ጉዞ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ይደረግባቸዋል

93
አዲስ አበባ ህዳር 30/2011 በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በተመለከተ ግንዛቤ ለማስጨበጥና የእግር ጉዞ ልምድን ለማበረታታትና ባህል ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ በማድረግ የጤናና አካል ብቃት ስፖርቶች ተካሄዱ። ዛሬ በመዲናዋ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ በማድረግ በተከናወነው የጤና የአካል ብቃት ስፖርቶች መርሃ ግብር የጤና ሚኒስትሩን ዶክተር አሚር አማንን ጨምሮ በርካታ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል። መርሃ ግብሩ በየወሩ የሚከናወንና በሌሎች የክልል ከተሞች የሚስፋፋ እንደሆነም ተጠቁሟል። በመዲናዋ መርሃ ግብሩ ሲከናወን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ አደባባዮችና ጎዳናዎች ዝግ ተደርገው ህብረተሰቡ በእግሩ እንዲጓዝ ተደርጓል። መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ የአዲስ አበባ መንገዶችን በወር አንድ ጊዜ የእግር ጉዞ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲደረግባቸው ለማስቻል እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። በሚቀጥለው አመት 15 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ለእግረኛ እና ለብስክሌት መንቀሳቀሻ ምቹ መንገዶችን ለመስራት መታሰቡን ጠቁመዋል። በየወሩ መጨረሻ እሁድ በመላው አገሪቱ በእግር የመጓዝ ልምድን ለማበረታታትና ባህል ለማድረግ መንገዶችን ለትራፊክ ዝግ እንደሚደረጉ ለማወቅ ተችሏል። በዛሬው መርሃ ግብር በርካታ ቁጥር ያላቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ  የእግር ጉዞና የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና አጋላጭ መንስኤዎቻቸውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲቻል ህብረተሰቡ የመመርመር ልምዱን እንዲያሳድግም ጥሪ ቀርቧል። በኢትዮጵያ በየአመቱ ከሚሞተው ሰው 52 በመቶው ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ምክንያት መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም