በትግራይ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው---የክልሉ ጤና ቢሮ

55
መቀሌ ህዳር 29/2011 በትግራይ ክልል ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። በሽታዎቹን መከላከልና መቆጣጠር ዓላማ ያደረገና "ከተሽከርካሪ ፍሰት ነጻ የሆነ ቀን" በክልሉ ሁሉም ከተሞች ነገ እንደሚከበር ተገልጻል። ይህን አስመልክትሞ በሽታዎቹን መካላከል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የመከረ መድረክ ትናንት በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተክላይ ወልደማርያም እንደገለጹት በክልሉ በልብ፣ በደም ብዛት፣ በስኳርና ካንሰር በመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ። በበሽታዎቹ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱንም አመልክተዋል። በመቀሌ ከተማ  በ2008 ዓ.ም አምስት በመቶ የነበረው በደም ብዛት የተያዙ የመንግስት ሠራተኞች ቁጥር  ዘንድሮ ወደ 18 በመቶ ከፍ ማለቱ በጥናት መረጋገጡን ለአብነት ጠቅሰዋል ። "በውስን ደረጃ ላይ የነበረው የስኳር በሽታ ስርጭትም ዘጠኝ በመቶ ደርሷል " ብለዋል ። አቶ ተክላይ እንዳሉት ለአብዛኛዎቹ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መነሻ ከሆኑ መካከል የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርዓት መጓደል፣ ጨው ያለመጠን መጠቀም፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የአልኮል መጠጥ ማብዛትና ሲጋራ ማጨስ ይጠቀሳሉ ። በሽታዎችን ለመከላከል የአመጋገብ ስርዓት ማስተካከልና በየጊዜው የአካል እንቅስቀሴ ማድረግ እንደሚገባም መክረዋል። "የበሽታዎቹን ስርጭት ለመግታት ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ ይሰራል" ያሉት ምክትል የቢሮው ኃላፊው በነገው እለት በክልሉ ሁሉም ከተሞች መንገዶችን ከተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ነጻ በማድረግ በሽታዎቹን የመከላከልና የመቆጣጠር መርሀ- ግብር እንደሚካሄድ አመላክተዋል ። በእለቱ በዋና ዋና መንገዶች ላይ ነጻ የህዝብ የእግር ጉዞና የአካል እንቅስቃሴ እንደሚካሄድ ገልፀው መርሀ ግብሩ በቀጣይም በወር አንድ ጊዜ እንደሚካሄድ ተናግረዋል ። "መርሀ ግበሩ የሚካሄደው ከተሽከርካሪ ነፃ የሆነ መንገድ በመጠቀምና የድምፅና የአየር ብክለትን በመቀነስ በጤና ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል ለህብረተሰቡ ለማስገንዘብ ነው" ያሉት ደግሞ የመቀሌ ከተማ ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ብርክቲ ገብረክርስቶስ ናቸው ። ህብረተሰቡ በየቀኑ ለ30 ደቂቃ የእግር ጉዞ በማድረግ እራሱን ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ጥቃት እንዲከላከል መነሳሳት መፍጠር የመርሀ- ግበሩ ዓላማ መሆኑንም ኃላፊዋ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም