ፋሲል ከተማ ደቡብ ፖሊስን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሻለ

100
አዲስ አበባ ህዳር 29/2011  በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታ ፋሲል ከተማ ደቡብ ፖሊስን 1 ለ ዜሮ በሆነ ውጤት አሸነፈ። በሀዋሳ ስታዲየም ዛሬ በተደረገው ጨዋታ ናይጄሪያዊው አጥቂ ኢዙ አዙካ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ፋሲል ከተማ አሸናፊ መሆን ችሏል። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚሰለጥነው ፋሲል ከተማ ነጥቡን ወደ ሰባት ከፍ በማድረግ ደረጃውን ወደ አራተኛ አሻሽሏል። እንዲሁም በዘላለም ሽፈራው (ሞሪኒዮ) የሚሰለጥነው ደቡብ ፖሊስ በሦስት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ፋሲል ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ በመሸነፍና አንድ ጊዜ አቻ ውጥቷል። በአንጻሩ ደቡብ ፖሊስ እስከ አሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፎ በሦስቱ ተሸንፏል። የአምስተኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ነገ በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይገናኛሉ። በክልል በሚደረጉ ጨዋታዎች በድሬዳዋ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማ ከደደቢት፣ በሀዋሳ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማ ከአዳማ ከተማና በሽሬ ስታዲየም ስሁል ሽሬ ከጅማ አባ ጅፋር በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ሲዳማ ቡና በ8 ነጥብ ሲመራ፤ ኢትዮጵያ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማና ፋሲል ከተማ በተመሳሳይ 7 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ስሁል ሽረ፣ ድሬዳዋ ከተማና ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ደረጃን በመያዝ ወራጅ ቀጠና ላይ ተቀምጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም