በኮፓ ኮካ ኮላ የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን ወደ ኬንያ ተጓዘ

50
አዲስ አበባ ህዳር 29/2011 ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የኮፓ ኮካ ኮላ የአፍሪካ አገራት ከ16 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን ዛሬ ወደ ኬንያ ተጓዘ። ውድድሩ በኮካ ኮላ ኩባንያ አዘጋጅነት ከታህሳስ 1 እስከ 6 ቀን 2011 ዓ.ም በኬንያ ርዕሰ መዲና ናይሮቢ ይካሄዳል። በሰሜን ምዕራብ ናይሮቢ በምትገኘው ናኩሩ አስተዳደር በሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ኢትዮጵያን ጨምሮ 12 የአፍሪካ አገራት ይሳተፋሉ። ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዛምቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ዚምባቡዌ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ሴኔጋል በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ አገራት ናቸው። የኮካ ኮላ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ብራንድ ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ትዕግስት ጌቱ ለኢዜአ እንደገለጹት 16 ተጫዋቾችን ጨምሮ 20 አባላት ያሉት ልዑክ ዛሬ ወደ ኬንያ አቅንቷል። ተጫዋቾቹ የተመረጡት የኮካ ኮላ ኩባንያ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ባካሄዳቸው የኮፓ ኮካ ኮላ ከ15 ዓመት በታች አገር አቀፍ የታዳጊ ውድድር ላይ የተሳተፉ ናቸው ብለዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የታዳጊ ተጫዋቾቹን ምልመላና መረጣ ያካሄደ ሲሆን የተመረጡት ተጫዋቾች በአገር አቀፉ ውድድር ላይ ጥሩ ብቃት ያሳዩ መሆናቸውን አስረድተዋል። ኮካ ኮላ በአፍሪካ አገራት በሚያካሂዳቸው ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ታዳጊዎች የውድድር ዕድል እንዲያገኙና ልምድ እንዲቀስሙ ታስቦ እንደሆነም ወይዘሪት ትዕግስት አመልክተዋል። በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ ቡድን ጥሩ ልምድ ያገኛል ተብሎ ይገመታል። እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1989 ጀምሮ በአፍሪካ ደረጃ በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊ የእግር ኳስ ውድድሮች ሲካሄድ እንደቆየ የገለጹት ወይዘሪት ትዕግስት አፍሪካን የሚያስጠሩ ኮከብ ተጫዋቾች ማፍራት የውድድሮቹ ግብ እንደሆነም ጠቁመዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የኮፓ ኮካ ኮላ የአፍሪካ አገራት ከ16 ዓመት በታች እግር ኳስ ውድድር በቀጣይም እንደሚካሄድ አመልክተዋል። በውድድሩ መርሃ-ግብር መሠረት በሰባት የውድድር ቀናት ቡድኖቹ በአራት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን የሚያካሂዱ ሲሆን ለአንድ ቀን ለተጫዋቾች የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና ይሰጣል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም