በመገናኛ ብዙሃን አሰራር ላይ የሚታዩ አፋኝ ህጎች ሊሻሻሉ ይገባል ተባለ

68
አዲስ አበባ ህዳር 29/2011 በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ልዕልናቸውን ጠብቀው እንዳይንቀሳቀሱ የሚያደርጉ  አፋኝ አሰራሮችና ክልከላዎች ሊነሱ ይገባል ተባለ። አዲስ የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑንም ተገልጿል። የጠቅላይ አቃቢ ሕግ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች  አማካሪ ጽህፈት ቤት በአገሪቷ ስላሉ ሚዲያ ሕጎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ተወያይቷል። የውይይቱ ዓላማ ከሕገ-መንግሥቱ ጀምሮ ከመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አሰራር ጋር በተያያዘ ያሉ አዋጆች ያሉባቸውን ችግሮች  የተመለከተ ግብዓት ማሰባሰብ ነው። በጠቅላይ አቃቢ ሕግ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች  አማካሪ ጽህፈት ቤት የመገናኛ ብዙሃን ሕጎች ጥናት ቡድን ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ጎሹ በዘርፉ የሚስተዋሉና በጥናት የተለዩ ክፍተቶችን የሚያትት ጥናት አቅርበዋል። በጥናቱም ሀሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጋር በተያያዘ የተጣሉ ገደቦች፣ የመረጃ ነጻነት ሕግ አፈፃፀም ላይ ያሉ ተጽዕኖዎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተብራርቷል። ቅድመ ምርመራ ወይም ሳንሱር ማድረግ በሕገ መንግሥቱ የተከለከለ ቢሆንም በተግባርና በአንዳንድ ዝርዝር የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ተግባራዊ መደረጉ ሊታረም የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም አክለዋል። አቶ ሰለሞን በጥናታቸው እንዳሉት ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ህጎች በአገር ውስጥ ከወጡ መሰል ህጎች ጋር በአግባቡ አጣጥሞ መተግበር ላይ ክፍተት አለ። መገናኛ ብዙሃንን የሚመሩት ሕጎች የተበታተኑና ወጥ አለመሆናቸውም በዘርፉ አሰራር ላይ የሚታዩ ሌሎች ችግሮች መሆናቸውንም  አብራርተዋል። ''የመረጃ ነጻነት አዋጁ በርካታ ክልከላዎችን ከመያዙም በላይ ክልከላዎቹም አሻሚና በተፈለገው መንገድ ሊተረጎሙና ጥቅም ላይ ሊውሉ መቻላቸው ቁልፍ ከሚባሉት የዘረፉ ፈተናዎች መካከል ናቸው" ሲሉም አስረድተዋል። በመሆኑም ከመገናኛ ብዙሃን አሰራር ጋር በተያያዘ በሥራ ላይ የሚገኙ ህጎችንና አዋጆችን የመመርመር ተግባር ተጀምሯል። ቡድኑ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች በመቃኘት ህጎቹ በአዲስ መልክ የሚቀረቁበትን ወይም አንዲሻሻሉ የሚደረጉበትን መንገድ ይቀይሳል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሚሻሻለው የሚዲያ አዋጅና ህጎች ላይ ቢካተቱ መልካም ነው ያሏቸውን ነጥቦች አካፍለዋል። ጦማሪ በፍቃድ አባይ በሰጠው አስተያየት "የተለያዩ የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች ከማተሚያ ቤቶች ጀምሮ አፈና ይደረግባቸዋል፤ ይህም ከስርጭት ውጪ እያደረጋቸው ነው" ብሏል። በዚህ ምክንያት አሳታሚዎች ለኪሳራ ሲዳረጉ ቆይተዋል ያለው በፍቃዱ ''ለሚደርስባቸው ኪሳራ ተገቢ ካሳ እንኳን አይታሰብላቸውም፤ በቀጣይ ይህን የመሰለው ጉዳይ ዋስትና ሊያገኝ ይገባል'' ሲል ተደምጧል። የመንግሥት ሕዝብ ግንኙነት ስራም ቢሆን መገናኛ ብዙሃንን መርጠው የመስጠት እንደሚስተዋልበቸው የገለጸው ጦማሪው "ይህም መረጃ ከማግኘት መብት ጋር የሚጣረስ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ሊያገኝ ይገባዋል" ሲል አሳስቧል። ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የተወከሉት አቶ ቶሌራ ፍቅሩ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን መቀጨጭ ዋናው ምክያት ተቋማዊ ድጋፍ አለመኖር እንድሆነ ይናገራሉ። ለባለሙያዎች ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ በመስጠት መደገፍ ያስፈልጋል በማለት አቶ ቶሌራ አሳሰበዋል። የመድረክ ፓርቲ ተወካይ አቶ ሙላቱ ገመቹም በበኩላቸው በኢትዮጵያ ሚዛናዊ ዘገባ የሚያቀርብ መገናኛ ብዙሃን አለመኖር ቁልፍ የዘርፉ ችግር ነው በማለት ተከራክረዋል።   "የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባር የጎደላቸው መሰል አዘጋገቦች በሕግ ማዕቀፍ የሚታዩበት ስርዓት ቢኖር የተሻለ ነው" የሚል ሀሳብ አንጸባርቀዋል። ከራዕይ ፓርቲ የመጡት አቶ ተሻለ ሰብሮ ደግሞ ''ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በተያያዘ በሕገ - መንግስቱ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ሳይስተካከሉ የሚዲያ ሕግ ማሻሻያ ላይ ማውራት ከፈረሱ ጋሪው የመቅደም አይነት ነው'' ያላሉ።   ''ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገቢውን የአየር ሽፋን እያገኙ አይደለም'' ያሉት ደግሞ የመኢአድ ዋና ጸሃፊ አቶ ዘመኑ ሞላ ናቸው።   አቶ ዘመኑ አክለውም፤ "በተለይ በምርጫ ክርክር ወቅት ሀሳባችን ይቆረጣል፤ ይህም የዲሞክራሲ ምህዳሩን የሚያጠብ በመሆኑ ሊጤን ይገባል" ብለዋል። የቡድኑ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን በሰጡት ማጠቃለያ የአዘጋገብ ስነ -ምግባርን በተመለከተ በቀጣይ በሚደረገው የህግ ማሻሻያ ውስጥ የሚካተት መሆኑን ጠቁመዋል። አገሪቱ የምትመራበት አዲስ የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን የተናገሩት ሰብሳቢው የአቅም ግንባታ፣ የድጋፍና ክትትል ችግሮች በፖሊሲው አማካኝነት እየተመለሱ እንደሚሄዱ ነው ያብራሩት። የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ወቅት ድምጻቸው መሰማት አለበት የሚል አቋም በመንግስት በኩል መኖሩን ጠቅሰው ጉዳዩ ወደፊት በዝርዘር በሚወጣ መመሪያ ይታያል ሲሉም አክለዋል። ማህበራዊ ሚዲያውና የጥላቻ ንግግር/ሄት ስፔችን/ለማስተዳደር የተለያዩ አገራት ተሞክሮ እየታየ መሆኑን ገልጸው ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፎችን ለማውጣት ውይይት እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም