ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የትግራይ ህዝብ ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋል-ዶክተር ደብረጽዮን

54
መቀሌ ህዳር 29/2011 ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን ያልተቆጠበ ጥረት እንደሚያደርግ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ። “ህገ-መንግስቱና የህግ የበላይነት ይከበር” የሚል መልዕክት የተንጸባረቀበት ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል። በህዝባዊ ሰልፉ ላይ የተገኙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ህገ መንግስቱ የሁሉም የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህልውና ዋስትና በመሆኑ ሊከበር እንደሚገባ ገልጸዋል። መላው የአገሪቱ ህዝቦችም ህገ-መንግስቱን ለማክበርና ለማስከበር በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባም ነው ያመለከቱት። “በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የህግ ጥሰት በስፋት ይታያል” ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን በእዚህም ዜጎች በማንነታቸው ለጥቃትና ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም በቀጣይ አገሪቱ ወደባሰ አለመረጋጋትና ቀውስ ውስጥ ከመግባቷ በፊት ለሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች ዋስትና ለሆነው ህገመንግስት መከበር የአገሪቱ ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል። የትግራይ ህዝብ  እንደ ትናንቱ ሁሉ ችግሮችን በመቋቋም ሰላም የሰፈነባት፣ ዴሞክራሲ የነገሰባትና በዓለም የምትጠቀስ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከሌሎች ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን ያልተቆጠበ ጥረቱን ዛሬም እንደሚያደርግ ዶክተር ደብረጽዮን አረጋግጠዋል። ከህዝብ ለሚቀርቡ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ተገቢ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ገልጸው፣ የፌደራል ስርአቱን ለማፍረስ የሚጥሩ ኃይሎችን ሥርአት ማስያዝ እንደሚገባ አሳስበዋል። “ከእዚህ በኋላ ህግ መንግስታዊ ጥሰት ሊቀጥል አይገባም” ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለውን ያለመረጋጋት ችግር ህዝቡ እንደትናንቱ በትእግስት፣ በአስተዋይነትና በብልሀት ሊፈታው እንደሚገባ አመልክተዋል። የትግራይ ህዝብና መንግስት ለሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች የላቀ ክብር ያላቸው መሆኑንም ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ከጎኑ ሆኖ ለተሰዋውና ብዙ ችግሮች ላሳለፈው የአማራ ህዝብ የላቀ ክብር እንዳለው የተናገሩት ዶክተር ደብረጽዮን፣ “ሁለቱን ህዝቦች ደም ለማቃባት ጥረት የሚያደርጉ ጽንፈኞችን ህዝቡ ሊታገላቸው ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል። ኤርትራዊያንም በሁለቱ አገራት መካከል በአሁን ወቅት የተፈጠረውን ሰላም ተጠቅመው ያለፈውን ማካካስ በሚያስችል መልኩ በክልሉ ያለስጋት ተንቀሳቅሰው  እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ወጣቶች በርካታ ችግሮችን ተቋቁመው የህገመንግስት ጥሰትን ለመከላከል በማህበራዊ ሚዲያና ሌሎች መድረኮች እያደረጉት ያለውን ጥረትንም ዶክተር ደብረጽዮን አድንቀዋል። ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ደስታ ተክሉ እንደገለጹት በተለያየ ደረጃ እየተስተዋለ ያለው የህግ ጥሰት በመንገስት ተገቢ ትኩረት እንዲያገኝ ድምጻቸውን ለማሰማት  ሰልፍ መውጣታቸውን ገልጸዋል። ዜጎች ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው ችግር እየገጠመው መሆኑንና በተለይ ሴቶች በግጭት ወቅት ይበልጥ ተጎጂዎች ስለሆኑ ይህ እንዲቆም ለመጠየቅ ሰልፍ እንደወጡ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ እየሩሳሌም ተስፋማሪያም የተባሉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም