ድሬዳዋ ከነማ በሁለቱም ጾታዎች የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር አሸናፊ ሆኗል

61
አዲስ አበባ ህዳር 29/2011 ድሬዳዋ ከነማ የዓመቱ የመጀመሪያው የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር  አሸናፊ ሆነ። ክለቡ በሁለቱም ጾታዎች ነው የ2011 የመጀመሪያው ብሄራዊ ቦክስ ክለቦች አሸናፊ የሆነው። በድሬዳዋ ከተማ ከህዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው ውድድር ዛሬ ተፈፅሟል። በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከ7 ክለቦች የተወጣጡ ከ80 በላይ ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል። አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ማራቶን፣ ድሬዳዋ ከነማ፣ ወላይታ ጦናና ሃላባ በውድድሩ የተሳተፉ ክለቦች ናቸው። ውድድሩ በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም፤ በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም የክብደቶች ዘርፍ ተካሂዷል። የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ዛሬ በተጠናቀቀው ውድድር ድሬዳዋ ከነማ በሁለቱም ጾታዎች አሸናፊ ሆነዋል። በወንዶች ድሬዳዋ ከነማ፣ ፌደራል ፖሊስና ማራቶን ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ የያዙ ሲሆን በሴቶች ድሬዳዋ ከነማ፣ አዲስ አበባ ፖሊስና ወላይታ ጦና ከአንድ አስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። ክለቦቹ ደረጃውን ያገኙት በውድድሩ ባገኙት የሜዳሊያ ብዛት እንደሆነም አስረድተዋል። ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ሁለተኛው ውድድር በጥር ወር 2011 ዓ.ም በወላይታ፤ ቀሪዎቹ ሁለት በጅግጅጋና አዲስ አበባ ይካሄዳል። በአራቱም ብሔራዊ የቦክስ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ቡድኖች ውጤት ተደምሮ የ2011 ዓ.ም የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚሆኑም ነው አቶ ስንታየሁ ያስረዱት። የውድድሩ ዓላማ ተተኪ ቦክሰኞችን መመልመልና ብቁ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት ነው ተብሏል። ከዚህም ሌላ በዓመቱ መጨረሻ በሞሮኮ ለሚካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን የሚወክሉ የቦክስ ተወዳዳሪዎችን መምረጥም ሌላው የውድድሩ ዓላማ መሆኑን አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል። በወንዶች ፌዴራል ፖሊስ በሴቶች ደግሞ አዲስ አበባ ፖሊስ የ2010 ዓ.ም የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር አጠቃላይ አሸናፊ መሆናቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም