በሁለተኛው የታዳጊ ወጣቶች ቅርጫት ኳስ ሻምፒዮና በወንዶች አዲስ አበባ በሴቶች ኦሮሚያ ክልል አሸናፊ ሆኑ

55
አዲስ አበባ ህዳር 29/2011 በሁለተኛው አገር አቀፍ የስፕራይት ቦለርስ የታዳጊ ወጣቶች የቅርጫት ኳስ ውድድር በወንዶች አዲስ አበባ በሴቶች የኦሮሚያ ክልል አሸናፊ ሆነዋል። ከህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ራስ ኃይሉ የስፖርት ማዕከልና ትንሿ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው ውድድሩ ዛሬ በትንሿ ስታዲየም ፍጻሜውን አግኝቷል። ውድድሩ የተካሄደው ከትምህርት ቤት የተመለመሉና ዕድሜቸው ከ17 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች መካከል ነው። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጥበቡ ቸኮል ውድድሩ ለታዳጊ ወጣቶች የውድድር አማራጭ ለመፍጠርና ልምድ እንዲያገኙ ታስቦ የተዘጋጀ ውድድር ነው ብለዋል። ዘጠኙ ክልሎችና ሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ከኮካ ኮላ ኩባንያ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ባለፈው በየክልላቸው ውድድሩን አካሂደው በአገር አቀፍ ደረጃ የመዝጊያ ውድድሩ ከህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ መቆየቱንም ጠቅሰዋል። በወንዶች የአማራና የትግራይ ክልል እንዲሁም በሴቶች የሶማሌ ክልል በአዲስ አበባው ውድድር ላይ እንዳልተሳተፉና ላለመሳተፋቸው ምንም ምክንያት እንዳላቀረቡ የተገለጸ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ያልተሳተፉበትን ምክንያት በግልጽ እንዲያሳውቁ እንደሚያደርግም አስረድተዋል። የኮካ ኮላ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ብራንድ ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት ትዕግስት ጌቱ በበኩላቸው በውድድሩ ብቁ የሆኑ ታዳጊዎችን በመመልመል ለወደፊት እድገታቸው የሚያስፈልጋቸው ስልጠናና ድጋፍ እንደሚደረግ አመልክተዋል። ውድድሩ ቀጣይነት እንደሚኖረውና በትምህርት ቤቶችም ውድድሩ እንዲካሄድ እቅድ መያዙን ጠቁመዋል። ኮካ ኮላ ከቅርጫት ኳሱ በተጨማሪ በእግር ኳሱም የኮፓ ኮካ ኮላ ውድድርን በማዘጋጀት ስፖርቱን እያገዘ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ዛሬ በሁለቱም ጾታዎች የፍጻሜ ጨዋታዎች ተካሂደዋል። ጠንካራና ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበትና የተመልካችን ቀልብ በሳበው የወንዶች የፍጻሜ ጨዋታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኦሮሚያ ክልልን 34 ለ 30 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በተመሳሳይ በሴቶች የፍጻሜ ጨዋታ የኦሮሚያ ክልልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያገናኘ ሲሆን በውጤቱም የኦሮሚያ ክልል 34 ለ 24 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በጨዋታው የኦሮሚያ ክልል የበላይነት በከፍተኛ ሁኔታ የታየበት ነበር። በሁለቱ የፍጻሜ ጨዋታዎች ላይ ከቅርብ ርቀት ቅርጫት የማስቆጠር፣ ጊዜን ጠብቆ ለቡድን አጋር ኳስ ማቀበል፣ ኳስን ረጅም ጊዜ ማቆየትና አወራወር ላይ በተጫዋቾች በኩል ክፍተት የታየ ሲሆን የተጫዋቾችን ቴክኒካዊ ብቃት ማጎለልበት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው። በአጠቃላይ በወንዶች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣የኦሮሚያ ክልልና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ የያዙ ሲሆን በሴቶች ፣የኦሮሚያ ክልል፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የጋምቤላ ክልል ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። በወንዶች የአዲስ አበባው አሸናፊ ሃይለ ስላሴ ኮከብ በሴቶች የኦሮሚያዋ ህይወት ብዙዋየሁ ኮከብ ተጫዋች ሆነው ተመርጠዋል። በወንዶች ኤርሚያስ ንጉሴ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሴቶች አሰግድ ተስፋዬ ኮከብ አሰልጣኝ ሆነዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮቹ አሸናፊ ሃይለ ስላሴና መስከረም ታደሰ በቅደም ተከተል የውድድሩ ኮከብ የሶስት ነጥብ አስቆጣሪ በሚል የተመረጡ ሲሆን በወንዶች የጋምቤላ ክልል በሴቶች የሐረሪ ክልል የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል። በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑት አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በኮከብነት የተመረጡ አሰልጣኝነትና ተጫዋቾች የዋንጫ ሽልማት ከኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽንና ከኮካ ኮላ ኩባንያ የስራ ሃላፊዎች ተበርክቶላቸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም