የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀንን የኋሊት

332
አዲስ አበባ  ህዳር 29/2011 የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዝያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሔደው ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ ህገ-መንግስቱ የጸደቀበት ህዳር 29 የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ወሰነ። ውሳኔው የኢትዮጵያ ህዝቦች መክረውና ፈቅደው ያጸደቁት ህገ-መንግስት ያስገኘላቸውን ጥቅሞች እንዲያስቧቸው፤ መብቶችና ነጻነቶቻቸውን ጠብቀው ማቆየት ብቻ ሳይሆን እርስ በእርስ ማስተዋወቅና ማስተሳሰር እንዲችሉ ለማድረግ ነው። የመጀመሪያው የብሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በ1999 ዓ.ም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ የተከበረ ሲሆን መሪ ሀሳቡም ''ሕገ-መንግስታዊ ቃል ኪዳን የአብሮነታችን መገለጫ ነው'' የሚል ነበር። ሁለተኛው በዓል ደግሞ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም በ2000 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መዲና በሆነችው ሀዋሳ ''ልዩነታችን ውበታችን ውበታችን አንድነታችንና ጥንካሬያችን ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል። ሶስተኛው በዓል ደግሞ በ2001 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ የተከበረ ሲሆን መሪ ሀሳቡም ''ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን በማጠናከር ልማታችንን እናፋጥናለን''  የሚል ነው። በ2002 ዓ.ም አራተኛው በዓል በድሬደዋ አስተዳደርና አጎራባች ክልሎች ማለትም ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ሀረሪና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን ''መቻቻል ለዴሞክራሲያዊ አንድነትና ልማት'' በሚል መሪ ሀሳብ በድሬዳዋ ተከብሯል። አዲስ አበባ ከተማ በ2003 ዓ.ም አምስተኛውን በዓል በድጋሜ ለማዘጋጀት ዕድሉን ያገኘች ሲሆን ''የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እጅ ለጅ ተያይዘን የአገራችንን ህዳሴ ወደማይቀለበስበት ደረጃ እናደርሳለን'' የሚል መሪ ሀሳብ ነው ጎልቶ የተሰማው። ስድስተኛው የብሔሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በትግራይ ክልል አዘጋጅነት በመቀሌ በ2004 ዓ.ም ተከብሯል፤ መሪ ሀሳቡም ''ሕገ መንግስታችን ለብዝሃነታችን ለአንድነታችንና ለሕዳሴችን'' የሚል ነበር፡፡ በአማራ ክልል አዘጋጅነት በ2005 ዓ.ም ''ብዙም አንድም ሆነን በመለስ ራዕይ በሕገ-መንግስታችን ለሕዳሴያችን'' በሚል መሪ ሀሳብ ሰባተኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በባህር ዳር ተከብሯል። ስምንተኛው የብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ደግሞ በሶማሌ ክልል አዘጋጅነት በጅግጅጋ ''ሕገ-መንግስታችን ለህዳሴያችን'' በሚል መሪ ሀሳብ በ2006 ዓ.ም ተከብሯል። በቤንሻንል ጉምዝ ክልል በአሶሳ ከተማ በ2007 ዓ.ም የተከበረው ዘጠነኛው የብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ''በህገ-መንግስታችን የደመቀው ኢትዮጵያዊነታችን ለህዳሴያችን'' በሚል መሪ ሀሳብ ነበር የተከበረው። 10ኛው የብሄር፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በጋምቤላ በ2008 ዓ.ም የተከበረ ሲሆን መሪ ሀሳቡም ''የብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተሳትፎ ለላቀ እድገትና ትራንስፎርሜሽን'' በሚል መሪ ሐሳብ ነበር የተከበረው። 11ኛው የብሔርሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልም እንዲሁ ''ህገ- መንግስታችን ለዲሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴያችን'' በሚል መሪ ሀሳብ በ2009ዓ.ም በሐረር ተከብሯል። 12ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን "በሕገ-መንግስታችን የደመቀ ህብረ-ብሔራዊነታችን ለህዳሴያችን" በሚል መሪ ሃሳብ በአፋር ዋና ከተማ ሰመራ ነው የተከበረው። የዘንድሮው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አዲስ አበባ ለሶስተኛ ጊዜ እያስተናገደች ሲሆን የበዓሉ መሪ ሀሳብም ''በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት''የሚል ነው። በዓሉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በራሳቸውና በተወካዮቻቸው አማካኝነት እርስ በእርስ የሚተዋወቁበት፣ ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት፣አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበት፣ የጋራ እምነቶቻቸውንና ተስፋቸውን የሚጋሩበት ቀን ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም