ሆስፒታሎቹ ቆሻሻ የሚያስወግዱት ለጤና አደገኛ በሆነ ኋላቀር መንገድ መሆኑ ተገለፀ

84
አዲስ አበባ ህዳር 29/2011 በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት ሆስፒታሎች የቆሻሻ ማቃጠያ መሳሪያዎቻቸው በመበላሸታቸው በአሁኑ ወቅት ቆሻሻ የሚያስወግዱት ለጤና አደገኛ በሆነ ኋላቀር መንገድ መሆኑን ገለፁ። የዘውዲቱ መታሰቢያ እና የራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታሎች ከዚህ በፊት ይጠቀሙበት የነበረው የቆሻሻ ማስወገጃ መሳሪያ በዓለም ጤና ድርጅት በእርዳታ የተገኘና "ኢንሲኒሌተር" በሚል የሚታወቅ ጭስ አልባ ዘመናዊ ማሽን ነው። ይህ  መርፌን ጨምሮ የህክምና አገልግሎት ሰጥተው በቆሻሻ መልክ የሚወገዱ ቁሳቁሶችን ወደአመድነት የመቀየር አቅም ያለውና ጤንነቱ የተጠበቀ  የህክምና ድባብ ለመፍጠር የሚያግዝ ዘመናዊ መሳሪያ ነው። ቆሻሻ ሲቃጠል የሚወጣው ጭስ ሳይሆን እንፋሎት በመሆኑ ቆሻሻ የማስወገድ ተግባሩ አካባቢን ከብክለት ይከላከላል፤ በአካባቢው ማህበረሰብ ሊፈጠር የሚችልን የጤና ጉዳትም ያስቀራል። ማሽኑ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶችን ጨምሮ ከፍተኛ ክምችት ያለውን ቆሻሻ በአንድ ዙር የማቃጠል አቅም አለውም ተብሏል። አስከ ከ8 ሺህ ዶላር እንደሚያወጣ የተነገረለትን የቆሻሻ ማስወገጃ መሳሪያው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ሆስፒታሎቹ በእርዳታ ያገኙት። ከዓለም ጤና ድርጅት የተበረከቱት ማሽኖቹ አገልግሎት መስጠት የቻሉት ግን ለአንድ አመት ብቻ እንደሆነ የሚገልፁት ሆስፒታሎቹ በአሁኑ ወቅትም ማሽኖቹ ላይ ደረሰ በተባለው ብልሽት ምክኒያት አገልግሎታቸው መቆሙን ገልፀዋል። በሆስፒታሎቹ የተገኘችው የኢዜአ ሪፖርተርም ማሽኖቹ አገልገሎት መስጠት ማቆማቸውን ታዝባለች። በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የጤና አጠባበቅ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ረጋሳ ማሽኑ በመዲናዋ ለሚገኙ ሆስፒታሎች ሲከፋፈል ሆስፒታሉም ተረክቦ እንደነበር አስታውሰዋል። መሳሪያው የሌላቸው የጤና ተቀማት ጭምር መወገድ ያለባቸውን የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችና ሌሎች ቆሻሻዎችን እንዲያቃጥሉ ከማስቻሉም ባሻገር ከተማ አስተዳደሩም ለቆሻሻ ማቃጠያነት ሲጠቀምበት መቆየቱንም ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ይህ ማሽን ከአንድ አመት የዘለለ የአገልግሎት መስጠት ተስኖት ለብልሽት በመዳረጉ በአሁኑ ወቅት ያለምንም ጥቅም ቆሟል ይላሉ ባለሙያው። በዚህ ምክኒያትም በቀድሞው ኋላ ቀር የማቃጠያ ዘዴ መጠቀም ግዴታ ሆኗል ሲሉ አክለዋል። የራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ንኡስ የስራ ሂደት መሪ አቶ እስክንድር አያሌው እንደገለጹት ሆስፒታሉ ኢንስኒሌተሩን በወቅቱ ሲረከብ አስፈላጊው የመለዋወጫ እቃና ሙያተኛ አልነበረውም። በዚህም ከእንግሊዝ አገር የመጡ ሙያተኞች መሳሪያውን በመገጣጠም ለአገልግሎት ዝግጁ ቢያደርጉትም ስራ ላይ በነበረበት ወቅት ተያያዥ ችግሮች እንደነበሩበት አውስተዋል። በሆስፒታሉ ከ350 እስከ 450 ኪሎ ግራም የሚመዝን ቆሻሻ በየቀኑ የሚመረት መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው መሳሪያው ይህንን በዘመናዊ መንገድ ለማስወገድ እያገዘ ነበር ብለዋል። ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ስራውን ሙሉ በሙሉ አቁሟል ነው ያሉት። የሆስፒታሎቹ ባለሙያዎች ከቆሻሻ ማስወገጃ ማሽኑ ጋር በተያያዘ ስላጋጠመው ችግር የከተማዋ ጤና ቢሮ ምንም አይነት ክትትልና ድጋፍ እያደረገ አለመሆኑን ይገልፃሉ።  አንስተዋል። የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ በበኩሉ ማሽኖቹ ከአለም የጤና ድርጅት በእርዳታ መልክ የተገኙ በመሆናቸው መለዋወጫው በቀላሉ በአገር ውስጥ ማግኘት አልተቻለም፤ ይህም ችግሩን በአጭር ግዜ ለመፍታት ውስብስብ አድርጎታል ብሏል። የጤና ቢሮው ምክትል ኃላፊ ዶክተር ሳሙኤል ዘመንፈስቅዱስ እንደገለጹት ማሽኖቹን የለገሰው የአለም የጤና ድርጅት በወቅቱ መለዋወጫዎችን ከመሳሪያው ጋር ባለመስጠቱ ነው የማሽኖቹን ብልሽት ለመጠገን አዳጋች የሆነው። ችግሩን ለመፍታትም መለዋወጫውን በግዥ ለመፈጸም ለአቅራቢ ድርጅቶች ጨረታ የወጣ ቢሆንም ምንም አይነት ድርጅት በጨረታው ለመሳተፍ ፍላጎት ባለማሳየቱ ጨረታውን ውድቅ ለማድረግ መገደዳቸውንም ምክትል ኃላፊው አክለዋል። በዚህም እርዳታውን ላበረከተው ድርጅትና መሳሪያውን ላመረተው ኩባንያ ችግሩን በማሳወቅ መሳሪያዎቹ መልሰው አገልገሎት ላይ እንዲወሉ ለማድረግ እየተሞከረ ነው ይላሉ። የኢዜአ ሪፖርተር መገንዘብ እንደቻለችው የቆሻሻ ማስወገጃ መሳሪያው ሥራ ካቆመ ከአንደ ዓመት በላይ ጊዜ አስቆጥሯል። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሎቹ የተገለገሉባቸውን የህክምና ቁሳቁሶችና ሌላ ቆሻሻ የሚያስወግዱት ለጤናና የአየር ብክለት አደገኛ በሆነ፤ ጊዜ ያለፈበት ዘዴ በቀጥታ በማቃጠል ነው።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም