ኢትዮጵያችን መንትያና ምትክ የሌላት አንዲት ሀገራችን ናት - ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ

114
ህዳር 28/2011 ኢትዮጵያ መንትያና ምትክ የሌላት  የሁሉም ኢትዮጵያዊ  አንዲት ሀገር መሆኗን የኢፌዲሪ  ጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር አቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ  የብሔር ብሔረሰቦች (የኢትጵያዊነት) ቀንን በማስመልከት  የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ሙሉ መልዕክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል ውድ የሀገሬ ሕዝቦች! ይህ ቀን የኢትጵያዊነት ቀን ነው። ይህ ቀን የኅብራዊ አንድነታችን ማክበሪያ ቀን ነው። ይህ ቀን ብዙዎች ስንሆን እንደ አንድ፣ አንድ ስንሆን እንደ ብዙ መሆናችንን የምናስብበት ቀን ነው። ይህ ቀን ሀገራችን አንድ፣ ጸጋዎቿ ግን ብዙ መሆናቸውን የምንገልጥበት ቀን ነው። አንድነትና ብዙነት ተፈጥሯዊ ነው። ሁለንታ (ዩኒቨርስ) ራሱ አንድ ሥርዓት ሆኖ፣ ነገር ግን በብዙ መልኩ የሚገለጥ ነው። አንዱ ሁለንታ (ዩኒቨርስ) በእልፍ አእላፍ ልዩ ልዩ ነገሮች የተሞላ ነው። ያ ባይሆንማ ኖሮ ዓለም ራሷ ልሙጥና አሰልቺ በሆነች ነበር። አንድና ልዩ ልዩ መሆን ለዓለም ጌጧ ብቻ አይደለም፤ ህልውናዋም የተመሠረተው አንድና ልዩ ልዩ ከመሆን ላይ ነው። ዓለም ጸንታ እንድትኖር ያደረጓት ልዩ ልዩ ፍጡራን እርስ በርስ እየተደጋገፉ፣ እየተዛመዱና እየተዋሐዱ ነው። በዕጽዋትና በእንስሳት መካከል ያለውን ተፈጥሯዊ ትሥሥር መመልከት ብቻ ለዚህ በቂ ነው። አንደኛው ለሌላኛው የህልውናው መሠረት መሆኑን በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። ኢትዮጵያችን መንትያና ምትክ የሌላት አንዲት ሀገራችን ናት። ኢትዮጵያዊነትም በብዙ ኅብር የሚገለጥ የዚህች ሀገር ዜጎች ድምር ጸጋችን ነው። አንዲቷ ኢትዮጵያ በብዙ ኅብርና በብዙ መልክ ነው የምትገለጠው። እነዚህ የአንድ አካል ልዩ ልዩ ክፍሎች የሆኑት  መልኮቿና ኅብሮቿ፣ ብሔርና ብሔረሰቦቿ ናቸው። ኢትዮጵያዊነት ደግሞ የሁሉም ድምርና ውሕደት ነው። ውሕደቱ ጠንካራ አንድነትን ይፈጥራል። አንድነት ስንል ግን “አንድ ዓይነትነት” ማለት እንዳልሆነ ሁሌም መረዳት ይኖርብናል። አንዳንዶች፣ እንደ ሕዝብ እየገጠሙን ላሉት ችግሮች መፍትሔው “አንድ ዓይነትነት” እንደሆነ ያስባሉ። አንድ ዓይነት መሆን ለችግሮቻችን ጊዚያዊም ሆነ ዘላቂ መፍትሔ ወይም ለጥንካሬያችን ዋስትና አለመሆኑን ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ ከጎረቤት ሀገራትታሪክ ልንማር እንችላለን። ብዝኃነት ጸጋ እንጂ እርግማን አለመሆኑን ሁላችንም መረዳት ይኖርብናል። ተፈጥሮም አንድ ዓይነትነትን አላስተማረችንም፡፡ አዳዲስ ጋሬጣዎችን ለማለፍ የሐሳብ ብዝኃነት ያስፈልገናል። ሐሳባችንን አዋሕደን በጠንካራ የሐሳብ ድልድይ በመሻገር ጋሬጣዎቻችን ለማለፍ የምናደርገው ጥረት ሀገር የመሆናችንን ትርጉም ያጎላዋል እንጂ አያቀጭጨውም። በተቃራኒው በትናንሽ ሐሳቦች ስንመራ የበለጠ እንኮስሳለን እንጂ የምናተርፈው ምንም ነገር አይኖርም። ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች ማወቃቸውን ለማሳየት የሚጣጣሩት ጸንቶ ከቆመው ግንብ ይልቅ ሽንቁሩን አጉልተው በመናገር ነው። ቀዳዳውን ከመድፈን ይልቅ ለማስፋት በመቆፈር ጊዜያቸውን ያጠፋሉ፡፡ “ትንሽ ማወቅ አደገኛ ነው” ይባላል፤ እውነትም ነው፡፡ በተንሸዋረረ መንገድ የተጀመረ ማወቅ ካለማወቅ ይብሳል፤ ሽንቁርን ብቻ እንድናይ ያደርጋልና። ብዙ እያወቅን ስንመጣ ግን ወደ አንድነት እንሳባለን፤ ወደ መተባበር እንመጣለን። ተደጋግሞ እንደሚባለው፣ ዕውቀት ወደ አንድነት ሲመራ ድንቁርና ግን ወደ መለያየት ይወስዳል። የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በረዥም የትሥሥር ዘመናቸው አጥር ሠርተው ቅጥር ተክለው የተቀመጡ አልነበሩም፤ አይደሉምም፤ ወደፊትም ሊሆኑ አይችሉም። ሲጋቡ፣ ሲዋለዱ፣ ሲዛመዱ፣ ሲወራረሱ፣ አንዱ ወደሌላው በግልም በወልም ሲሄዱ የቆዩ ናቸው። ዛሬ የአንዱ ባሕል አድርገን የምንናገረው ነገር፣ ያ ሕዝብ ጠብቆና አደራውን ይዞ ለኢትዮጵያ ያቆየላትን ባሕል ነው። ሀገር እንዳትጠፋ ያደረግነው፤ ጸጋዎቿንም ጠብቀናቸው የቆየነው ሁላችንም ተካፍለን ነው። ለዚህም ነው የአንዱ ባሕል የሁላችንም፤ የአንዱ ቋንቋ የሁላችንም፤ የአንዱ ዜማ የሁላችንም፤ የአንዱ አለባበስ የሁላችንም፤ የአንዱ ኑሮ የሁላችን ነው የምንለው። ያ ባሕል በዚያ ሕዝብ በኩል ተጠብቆ የኖረ የኢትዮጵያ ባሕል ነው። ሳይጠፋብን ተንከባክቦ፣ ሳንረሳው አስቦ፣ ሳይበላሽ ጠብቆ ስላቆየን፣ ሁላችን ነን ያንን ሕዝብ የምናመሰግነው። ሁሉም የእኛ ነውና። ከዘመናት በፊት እንዴት አብረን ስንኖር እንደነበር፣ እንዴት ስንወራረስ እንደኖርን ተረቶቻችን ታላቅ ምስክሮቻችን ናቸው። አዳዲሶቹ የጥላቻ ትርክቶች ከመምጣታቸው በፊት፣ አብረው የኖሩት ተረቶቻችን ምን ያህል እንደ ስፌት የተሣሠርን፣ እንደ ጥለት ያማርን፤ እንደ ቤተሰብ አብረን የኖርን፣ እንደ ማኅበረሰብ የተዛመድንና የተጋመድን መሆናችንን ይመሰክራሉ። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ኑሮና የሕይወት ዕጣ ፈንታ በቋንቋ ልዩነት ያልተቀነበበ፤ በሚጋሯቸው መልክአ ምድሮችና የተፈጥሮ ጸጋዎች ሁሉ አርብቶ በማደርና አርሶ በማምረት፤ በጋራ በገነቧቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተቋማትም ነግዶ በማትረፍ፤ ተክኖ በማነጽ፤ ሠልጥኖ በማበልጸግ፤ ተምሮ በማገልገል፤ በጠቅላላው ለፍቶ በማደር የተገናኙ፤ አንድ የሆኑ የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው። የአፍሪካውያንና የኢትዮጵያውያን ፍልስፍና መገለጫ የሆኑ ብዙዎቹ ሥነ ቃሎቻችን ከቋንቋቸው መለያየት ውጭ በይዘታቸውና በቅርጻቸው ተመሳሳይ ናቸው። ለብልኅ፣ ለተላላ፤ ለንጉሥ፣ ለወታደር፤ ለአለቃ፤ ለምንዝር፤ ለፈሪ፣ ለደፋር፤ ለቁጡ፣ ለታጋሽ፤ ለነቃሽ፤ ለአወዳሽ፤ ለታታሪ፣ ለሰነፍ፤ የምንወክላቸው የእንስሳት ገጻተ ባሕሪያት ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ጀግንነት፣ ለወገን ሟችነት፣ ታታሪነት፣ ብልሐት፣ ታጋሽነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ ወላጅ አክባሪነት፣ የሰውን አለመመኘት፣ አደራ ጠባቂነት፣ ታማኝነት፣ ቃልን አክባሪነትና ሌሎችም በተረቶቻችን ሁሉ የሚመሰገኑ ዕሴቶቻችን ናቸው። ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፣ ከኩርሙክ እስከ ቶጎ ጫሌ ብንሄድ እነዚህን ዕሴቶች በየተረቶቻችን ውስጥ እናገኛቸዋለን። በተቃራኒ ደግሞ ሌብነት፣ ነፍሰ ገዳይነት፣ ቅሚያ፣ ችኩልነት፣ ቃል አባይነት፣ ፈሪነት፣ ሀገር ሻጭነት፣ ከሐዲነት፣ በተረቶቻችን ውስጥ ይኮነናሉ፤ ይወገዛሉ። ኢትዮጵያችን ከሰጠችን ጸጋዎች አንዱ ብዙም አንድም ሆነን ለመኖር መቻላችን ነው። ብዙነታችን ሳይነጣጥለንና ሳይከፋፍለን፣ አንድነታችንም ሳይጠቀልለንና ሳይውጠን በዝተንና መልተን ኖረናል። አንድነታችን ለብዙነታችን ጥንካሬው ሆኖ፤ ብዙነታችንም ለአንድነታችን መገለጫው፣ ጌጡና ሀብቱ ሆኖ ኖረናል። አንድነታችን ለብዙነታችን ማሠሪያ ገመዱ፣ መቆሚያ ዓምዱ ነው። ብዙነታችን ደግሞ ለአንድነታችን ማንቀሳቀሻ ሞተሩ፣ ማዋቀሪያ ቋሚና ማገሩ ነው። ኢትዮጵያዊነት እንደ ወይን ጠጅ እያደር እያማረና እየጠነከረ የሄደው ብሔር ብሔረሰቦች ባሕላቸውን፣ ዕሴታቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ቅርሳቸውንና ታሪካቸውን የሚመግቡት በመሆኑ ነው። ኢትዮጵያዊነት እንደ ኩሬ ውኃ ጸጥ ብሎ የተኛ አይደለም። በብሔር ብሔረሰቦች መስተጋብር ምክንያት እንደ ባሕር የሚታደስ፤ እያደገ፣ እየዳበረና እየጠነከረ የሚሄድ የሕዝቦች ዕሴትና ሕልም ነው። በኢትዮጵያችን፣ ማንም ለማንም ባዳ አይደለም። በሚናገረው ቋንቋ የተለያየ ቢሆንም ‹ኢትዮጵያዊነት› የሚባል አንድ ቋንቋ ስላለውአንዱ ለሌላው ወገን ነው። የኛው ልጆች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተወልደው የዚያኑ ሀገር ቋንቋ ለምደውታል። በብዙ ነገራቸው የኛው ወገኖች ሆነው በባሕልና በቋንቋ ግን ከኛ ይለያሉ። ማንም ግን እነርሱን ባዕድ ናቸው አይልም። በሀገርም ውስጥ እንዲሁ ነው። በሌላ ቋንቋ የሚናገርና ሌላ ባሕልን የለመደ ወገናችን ነው - ያኛው። የእምነት ታሪኮቻችንም ሆኑ አፈ ታሪኮቻችን የሚነግሩን ወደ ኋላ ስንሄድ ግንዳችን አንድ መሆኑን ነው። እንግዳ ትርክቶችን ሰምተን ካልሆነ በቀር ባሕላችን የሚነግረን ሌላውን አክብረንና ወደን እንድንቀበለው ነው። በየቤታችን ‹እንግዳ› በጣም የተከበረ ነው። ‹ጥቁር እንግዳ› ማለት ደግሞ ከዚህ በፊት መጥቶ የማያውቅ አዲስ ሰው ነው። የማናውቀውን ሰው አክብረን ማስተናገድን እንጂ ገፍቶ ማባረርን ባሕላችን ፈጽሞ አያስተምረንም። በሁላችንም ባሕሎች ውስጥ ከኛ ባሕልና ቋንቋ ውጭ የሆኑ ወገኖችን የምንቀበልባቸው ባሕላዊ ሥርዓቶች አሉን፤ ተገፍቶ ለመጣ ሰው ጥብቅና የምንቆምባቸው ባሕላዊ ወጎች አሉን። አብሮን ለመኖር ለመጣ ሰው ከብሔረሰቡ አባል የበለጠ መብት የሚሰጡ ባሕሎች አሉን። ከሌላ ቦታ የመጣ ሰው ልጅ፣ ቤተሰብ፣ ወራሽ የሚሆንባቸው የከበሩ ሥርዓቶች አሉን። በዚህ መልኩ ስንደመር ነው የኖርነው። እኛ አንድም፣ ብዙም ነን። ኢትዮጵያን በጋራ ነው የመሠረትናት፤ በጋራ ነው ያቆየናት፤ በጋራ ነው የሞትንላት፤ በጋራ ነው ያስከበርናት፤ በጋራ ነው እዚህ ያደረስናት። የአንዱ ታሪክ የሌላችን ነው፤ የአንዱ መከራም የሌላችን ጭምር ነው። በአንደኛው ድንበር በኩል የመጣ ጠላት ወገናችንን ሲያጠቃ ‹ሆ› ብለን የዘመትነው፣ ያ ሕዝብ የአብራካችን ክፋይ ስለሆነ ነው። እርሱን መንካት እኛን መንካት መሆኑን ስለምናምን ነው። ‹አፍንጫ ሲመታ ዓይን እንደሚያለቅስ› የሚናገረው ብሂላችን ይህንኑ የሚያስረግጥ ነው። ከዚህ ታሪካችን፣ ባሕላችንና ልማዳችን ውጭ ጠላትነትን፣ ጥላቻን፣ መገፋፋትንና መራራቅን የሚዘሩብንን ኩሩው ባሕላችን አይታገሣቸውም። የዘሩትን እንነቅልባቸዋለን እንጂ እንዲያበቅሉት አንፈቅድላቸውም። ልዩነቶቻችንን አጉልተው፣ እንደ ገደል ያራራቀን ለሚያስመስሉት የአንድነት ታሪካችንንና ባሕላችንን ከፍ አድርገን እናሳያቸዋለን። ‹እንኳን ሰውና ሰው ጉልቻና ጉልቻ እንኳን ይጋጫል› ብለን የምንተርት ነንና ቅሬታዎችን በይቅርታ፣ ዝንፈቶችን በፍትሕ እናርማቸዋለን። የሚለያዩን ሲመስላቸው ይበልጥ እንደመራለን፤ የተቃረንን ሲመስላቸው ይበልጥ እንደ ድርና ማግ ተሣሥረን አንድ ሸማ እንሆናለን። ከግብርናው ባሕላችን እንደተማርነው ያለፉትን መልካሞቹን እንይዛለን፤ የስሕተት አረሞችንም በጋራ እናርማለን፡፡ እነሆ አዲሱን የለውጥ ጎዳና በመደመር መንፈስ ጀምረናል። ለውጡ በሕዝቡ ትግል ለሕዝቡ የመጣ ነው። ይህንን ተሥፋ ሰጭ ለውጥ የሰላም መደፍረስ፣ የብሔር ግጭቶች፣ የጅምላ ፍርድና ስሜታዊነት ለአደጋ እንዳያጋልጠው እንደ ሰጎን ዓይናችንን ሳንነቅል እንጠብቀዋለን። ኢትዮጵያ አምልጠውኛል ብላ በቁጭት የምትቆጥራቸው አያሌ ዕድሎች በቅርብም በሩቅ ዘመን አሏት። ይህየአሁኑም ከእነዚያ አንዱ እንዲሆን መፍቀድ የለብንም። አሳክተን ለልጆቻችን ማስረከብ ይጠበቅብናል እንጂ። ነገ የዚህ ለውጥ ስኬትታሪክ፣ ተረክና ተረት ሆኖ በየቋንቋችን መነገር እንዲችል ዛሬ የሚከፈለውን ሁሉ ከፍለን ከዳር ማድረስ አለብን። ይህ በዓል ለይስሙላ የምናከብረው ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የምናደርግበት ትርጉም ያለው በዓል ነው። ሁላችንም ‹ሆ› ብለን ወጥተን የኢትዮጵያዊነትን ልዩ ልዩ ጸጋዎች እያሳየን፣ እያከበርንና እየጠበቅን የምናከብረው የኅብራዊ አንድነታችን መገለጫ በዓል ነው። ልዩነቶቻችን የአንድነታችን ጸጋ፣ አንድነታችንም የልዩነቶቻችን ተደማሪ ዋጋ መሆኑን የምንገልጥበት ታላቅ በዓል ነው። መልካም ‹የኢትጵያዊነት በዓል› ይሁንልን። ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር! ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም