አብሮ መድመቅ ጎልቶ የታየበት የብሄር ብሄረሰቦች በዓል

80
አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 አብሮ መድመቅ ጎልቶ የታየበት የብሄር ብሄረሰቦች በዓል። ወጣት ኬላሊ ጋሹኒ ከወገብ በላይ እራቆቱን ሆኖ፣ ፊቱን ነጭ ቀለም ተቀብቶ ትኩረት በሚስብ አይነት አጊያጌጥ አሸብርቋል። በመዒኒት ቋንቋ እያዜሜ የሚቀበሉትና ዙሪያውን ከበው የሚጨፍሩት ግን አለባበሳቸው የአማራ የትግራይና ሌሎችም ብሄሮች ባህላዊ አለባበስ የተዋቡ ናቸው። ወጣቶቹ እሱ የሚያወርደውን ዜማ እየተቀበሉ ያጫፍሩታል፣ አጨፋፈሩንም ቢሆን ተክነውበታል፤ አለባበሳቸው ብቻ ነው የሚለየው። ጠጋ ብለን ስናነጋግራቸው የደቡብ ክልል የባህል አምባሳደሮች ናቸው። የዘንድሮ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የሚለየው እያንዳንዱ የየራሱን ብቻ ሳይሆን አንዱ የሌላውን በማጌጥ ከልዩነት ይልቅ አንድነት የሚጎላብትበት ሁነት መሆኑ ነው። ይህን ህብር ኢትዮጵያዊ የባህል ቡድን በአዲስ አበባ በሚከበረው 13ኛው የብሄሔሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ዋዜማ ላይ የጎዳና የባህል ትርዕት(ካርኒቫል) ሲያቀርቡ ነበር ያገኘናቸው። የአልባሳትና የጭፈራ ባህል ትርኢቱ ላይ ከታዩ ነገሮች ጎልቶ የወጣው ታዲያ ''የራሴ፣ የኔ'' ከማለት ይልቅ በአለባበስም በጭፈራም አንዱ የአንዱን እየቀላቀለ አብሮ መድመቅ ነው። ኢዜአ ያነጋገራቸው ኬላሊና ጓደኞቹም ይህንኑ ነው ያረጋገጡልን። ኬላሊ ጋሹኒ በሰጠው አስተያየት በ 13ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በአል ቋንቋና ባህል ወደ ሌላም እንዲሸጋገርና እንደ ኢትዮጵያ አንድ እንደንሆን ነው እንደዚህ በጋራ እየጨፈርን ያለነው ብሏል፡፡ ናርዶስ አያሌው በበኩሏ”አንድነታችንን ለማምጣት አስበን ነው፤ ያው ኢትዮጵያዊ ሲባል አንድ ነን፣ አሁን ካየኸኝ የለበስኩት የአማራን ብሄር ልብስ ነው ግን እየጨፈርኩ ያለሁት  የደቡብን ነው፤ ያ ማለት ያለውን ተስፋ ለማስቀጠልና ለአንድነታቸን ጠቀሜታ ስለአለው ነው።" በመድረኩ ላይ ያገኘናቸው ሌሎች ተሳታፊዎችም ትርኢቱን ስናሳይ ከራሳችን ባህል በላይ ህብረ ብሄራዊነትን ባማከለ መልኩ ነው ብለዋል። ከዚህ በኋላም በዓሉ ባህላችንን የምናስተዋውቅበት ብቻ ሳይሆን ባህል የምንወራረስበትና አገራዊ አንድነታችንን የምናጠናክርበት ሊሆን ይገባል ብለዋል። ''በመንገዱ ትርኢት እያሳየን ነው ያለነው፤ ይህ ትርኢት ደግሞ ህብረ ብሄራዊነትን የሚገልጽና በዚህ ህብረ ብሄራዊነት ጥልቅና እምቅ የሆነ የባህል አሴቶቻችን ከአንዱ ወደ አንዱ እያስተዋወቅን ነው ያለነው።'' ያለው መህመበ ሶደኔ ነው ካሳሁን ለማ በበኩሉ ''የባህል ትርኢቱን ዘንድሮ ትንሽ ለየት ባለ መልኩ ነው ያከበርነው። ሁላችንም በህብር ነው ስናክበር የነበርነው።  እርስ በእርስ ከወላይታ ጋር ከሲዳማ  ጋር  ከስልጤ ጋር ከሃላባ ጋር ፣ መሃል ላይ ደግሞ የሃድያ ባህል ይህን ይመስላል እያልን እያሳየናቸው ነው'' በፓናል ውይይት፣ በአውደ ርዕይ፣ በሙዚቃ ድግስ፣ በቡና ጠጡና ሌሎችም ዝግጅቶች ሲከበር የነበረው የዘንድሮው በዓልም ነገ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ይጠቃለላል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም