ሃገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ትምህርቶች ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ናቸው- የኃይማኖት አባቶች

73
ደሴ ህዳር 28/2011 ሃገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ትምህርቶች በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አለመሰጠት በዩኒቨርሲቲዎች ለሚያጋጥሙ ግጭቶች ምክንያት እንደሚሆን የደሴ ከተማና በአካባቢው የኃይማኖት አባቶች ገለጹ። የወሎ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል በግብርና ሚኒስትር ዲኤታ የተመራ የልዑካን ቡድን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል። በውይይት መድረኩ የተገኙት መላከ ሰላም አከለ ገላው እንደተናገሩት በአንደኛና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ታዳጊዎች የሚሰጣቸው ትምህርት ልዩነትን የሚያበረታታና አገራዊ አንድነትን የማያጠናክር ነው። ጥንት አባቶች ያለ ልዩነት አንድ ሆነው ጠላትን መመከትና ሃገርን በነጻነት ማቆየት መቻላቸውን ተናግረው ወጣቱ የሀገር ፍቅር እንዲኖረው በስፋት ስለ ሰላም፣ ፍቅር፣ ተከባብሮ ስለ መኖር ፋይዳ መማር እንደሚገባው ተናግረዋል። ስለዚህም መንግሥት ሥርዓተ-ትምህርቱን በመከለስ ትውልዱን ለሃገር ተቆርቋሪና ኃላፊነት የሚሰማው አድርጎ የመቅረጽ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀው እንደ ኃይማኖት አባትነታቸው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይሄን እንደሚያስተምሩ ገልጸዋል። ሌላው ተሳታፊ ሸህ ሰይድ አሊ በበኩላቸው "ሰላም የፈጣሪ ስም ነው፡፡ ስለ ሰላም ሲሰበክ አልቀበልም የሚል ፈጣሪውን እንደካደ ይቆጠራል" ብለዋል። ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት የዘለቀ የእምነት መሰረት እንዳላት ያስታወሱት ሸህ ሰይድ በየአምልኮ ቦታዎቹ ሰላምን አብዝቶ በመስበክ ልዩነትን ወደ አንድነት መቀየር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላዊን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት መምህር ጴጥሮስ ገብረስላሴ እንዳሉት በወሎ ዩኒቨርሲቲና አካባቢው አንጻራዊ ሰላም የሰፈነው የአስተዳደር በደል ስላልደረሰ ሳይሆን የህዝቡ የቆየ ተከባብሮ የመኖር ባህሉና ለሰላም ያለው ጽኑ እምነት መሆኑን ገልጸዋል። የኃይማኖት አባቶቹ በወሎ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ አባታዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር የላቀ ሚና ለተጫወቱ የኃይማኖት አባቶች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በአካባቢው ለረጅም ዘመናት ተከባብሮ የመኖር ባህል እንዲጎለብት፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር በማድረግ የኃይማኖት አባቶች የማይተካ ሚና መጫወታቸውን ሚኒስትር ዴኤታዋ አመልክተዋል፡፡ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ከውይይይቱ ጠቃሚ ግብአቶች እንደተገኙ ጠቁመው፤ ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ተማሪዎች መካከል የሶስተኛ ዓመት የነርሲንግ ተማሪ የሆነው አማረ መርሻ ሰላምን ማስከበር፣ ግብረ-ገብነትን ማጠናከርና ለሰው ልጆች ክብር መስጠት የሚኖረውን ፋይዳ ከውይይቱ መገንዘቡን ገልጿል። በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው በሚደረገው ጥረት በተማሪ ፖሊስነት ጸጥታ የማስከበር ስራዎችን ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ ተተማሪዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም