ለጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

76
ጋምቤላ ህዳር 28/2011 በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ቀጣይነት እንዲኖረው  የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ፡፡ ከፌዴራል ተቋማት የተውጣጡ የከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የልዑካን ቡድን ከዩኒቨርሲቲውና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል። ከልዑካን ቡድኑ አባላት መካከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ኡጁሉ ጊሎ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው ላለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሄደት ቀጣይነት የአካባቢው መህበረሰብ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል። ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ተገቢውን እውቀትና ክህሎት ይዘው መውጣት የሚችሉት ሰላለማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ሲኖር መሆኑን አቶ ኡጁሉ ተናግረዋል፡፡ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣የማህበረሰብና ኢንዱስትሪ ትስስር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክትር ጋልዋክ ጋርኮት በዩኒቨርሲቲ ያለው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ ከምንም በላይ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡ ተማሪዎችን በመደገፍና በመንከባከብ የአካባቢው ማህበረሰብ የተለመደውን ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል፡፡ በውይይቱ ላይ ከተገኙት የአካባቢው ማህበረሰብ መካከል ወይዘሮ ኙጌድ ኡዋር በሰጡት አስተያየት የክልሉ ተወላጅ ተማሪዎች በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በሰላም ተምረው እንደሚመለሱት ሁሉ  ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎች በሰላም ተምረው እንዲመለሱ የማደረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዳይኖር የሚፈልጉ አካላትን  ፈጣን እርምጃ በመውሳድ መከላከል እንደሚገባ  አስተያየት ሰጭዋ አሳስበዋል። በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት አቶ መቲያስ መሰኔ በበኩላቸው  ከሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ ጋምቤላ ዩኒቨርስቲ የመጡ ተማሪዎችን  ፍቅርና ድጋፍ በመሰጠት ትምህርታቸውን ያለምንም ስጋት እንዲከታተሉ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ቄስ ፍጹም ካሳይ  በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች ተከስቶ የነበረው የጸፅታ ችግር እንዳይከሰት ስለሰላም በማስተማር ለመማር ማስተማር ሂደቱ መጠናከር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ መጨረሻም ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚደግፍ የተማሪዎች፣  የከተማው ነዋሪዎች፣ የወጣት ማህበራት፣ የከተማ አስተዳደርና የዩኒቨረሲቲው ተወካዮች የተከተቱበት 11 አባል ያለው የሰላም ኮሚቴ ተቋቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም