የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ታሳሪዎች የፍርድ ቤት ቀጠሮ መንዛዛት እንዲስተካከል ጠየቁ

53
አዲስ አበባ ህዳር 28/2011 የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የቀጠሮና ፍርደኛ ታሳሪዎች   በምርመራ ወቅት የፍርድ ቤት የቀጠሮ መመላስ እንዲቀንስ በማድረግ ፍትህ የሚፋጠንበት ሥራ እንዲሰራ ጠየቁ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በስሩ ከሚያስተዳድረው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የቀጠሮና ፍርደኛ ታሳሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል። በውይይቱ የተሳተፉ የማረሚያ ቤቱ ታሳሪዎች የፍርድ ቤት ቀጠሮ እንደሚጓተት ጠቁመዋል። የቀጠሮ ታሳሪ የሆኑት አቶ በድሉ አሰፋ በቂ ማስረጃ ሳይሰበስቡ በቁጥጥር ስር ማዋል፣ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን በቀጠሮ ቀን አለማቅረብና በወቅቱ ክስ አለመመስረት ፍትህ እንዲዘገይና ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎች እንዲመላለሱ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህ ሁኔታ እንዲስተካከልና ፍትህ በአፋጣኝ መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በነበሩ መርማሪዎችና ፖሊሶች የመብት ጥሰት የተፈጸማባቸው ሰዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚቀላቀሉበትና የሚካሱበት ሁኔታ መንግስት ማመቻቸት እንዳለበት የገለጸው ሌላው አስተያየት ሰጪ ሰለሞን ገነቱ የተባለ ተጠርጣሪ ነው። መኮንን በየነ የተባለ ታሳሪ በሰጠው አስተያየት በማረሚያ ቤቱ በየቀኑ ሰው ስለሚገባ የመኝታ ጥበት፣ ፍርድ ቤቶች በአግባቡ የክስ መዝገቦችን እንዲመለከቱና ቀጠሮ አለማንዛዛት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት አለበት ሲል አስተያየት ሰጥቷል።   ሌላው አስተያየት ሰጪ ፍጹም ጌታቸው ደግሞ በአዲስ ዓመት ሁሉም ክልሎች በይቅርታ ታራሚዎችን ሲፈቱ በፌዴራል ደረጃ ይቅርታ እንዳልተሰጠ ጠቁሟል። ስለሆነም መንግስት የጀመረውን የይቅርታና ክስ የሟቋረጥ ሥራ በስፋት እንዲሰራ ተናግሮ በተለይም በቅርቡ ይከናወናል የተባለው ብሔራዊ እርቅ እስረኞችን አካታች እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲያደርጉበት ጠይቋል። ሌላው ታሳሪ አቶ ሸምሱ ሰይድ በበኩሉ መንግስት በውጭ አገሮች ያሉትን ዜጎች ለማስፈታት የሰጠውን ትኩረት ያህል ለአገር ውስጥ ታሳሪዎችም እንዲሰጥ ሲሉ ጠይቀዋል። በተለይም በአንድ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው በሂደት የሚለቀቁ ሰዎች፣ የክስ አቀራርብ፣ ፓርላማ የሚያወጣቸው የይቅርታና የምህረት አዋጆች አፈጻም ላይ ሰፋፊ ምልከታና ክትትል ቢደረግ ሲል አክሏል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የፍትህ ሂደቶች የህግ የበላይነትን መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲፋጠኑና እንዲረጋገጡ እንደሚሰራ ገልጿል። የምክር ቤቱ የህግ የፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ የስራ ቡድን መሪ አቶ አበበ ጎዴቦ እንደገለጹት፤ በአገሪቷ የህግ የበላይነትና የፍትህ ሂደቶች የተፋጠኑ እንዲሆኑ ቋሚ ኮሚቴው ይሰራል። በተለይ ፍትህ እንዳይዘገይ፣ የሀሰት ምስክሮች የሚመጡበት ሁኔታ እንዳይኖር፣ የቀጠሮ ምልልስ እንዲቀንስ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን የሚሰራው የክትትል፣ የቁጥጥርና ድጋፍ ሥራ በስፋት እንደሚከናወን ተናግረዋል። ዘርፉ ብዙ የህዝብ አቤቱታ፣ ሮሮ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በርካታ ባለድርሻ አካላትን የሚያቅፍ እንደሆነ ጠቅሰው ቋሚ ኮሚቴው የሚሰራው የክትትል፣ የቁጥጥርና የድጋፍ ሥራ ህግ በሚፈቅደውና የፍርድ ቤት ነጻነትን በማይነካ መልኩ ይከናወናል ሲሉ ገልጸዋል። ይህም በአገሪቷ እየመጣ ያለው ለውጥ በፍትህ ተቋማት፣ በማረሚያ ቤቶች፣ በፖሊስ ጣቢያና በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እንዲጎለብት በማድረግ የተጠርጣሪዎችና የታራሚዎች ሰብዓዊና ተጓዳኝ መብቶች እንዲጠበቁ ያስችላል ሲሉ አቶ አበበ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም