አትኩኝ የተሰኘ መጤ አረም በሰብልና በግጦሽ ማሳችን ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው - በጋምቤላ ክልል አበቦ ወረዳ አርሶ አደሮች

114
ጋምቤላ ህዳር 28/2011 በጋምቤላ ክልል አበቦ ወረዳ ሚሞሳ / አትኩኝ / የተሰኘ መጤ አረም በሰብልና በግጦሽ ማሳቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰባቸው መሆኑን የወረዳው አርሶ አደሮች ገለጹ ። የክልሉ ግብርና ምርምር ተቋም  አረሙን ለማጥፋት የሚያስችል ተስፋ ሰጭ ውጤት መገኘቱን አስታውቋል፡፡ አርሶ አደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት በአካባቢው የተከሰተው መጤ አረም በሰብልና በግጦሽ ማሳቸው ላይ ጉዳት እያደረሰባቸው ነው፡፡ በአበቦ ወረዳ የመንደር ሰባት ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ተፈራ ማርቆስ በሰጡት አስተያይት ሚሞሳ / አትኩኝ /  የሚባል መጤ አረም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋፈቶ በእርሻ ስራቸው ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአርሶ አደሮች አቅም አረሙን ለመቆጣጠር አለመቻሉን የገለጹት አርሶ አደሩ በአረሙ ምክንያት  ቀደም ሲል ያለሙት የነበረው ሶስት ሄክታር መሬት ወደ አንድ ሄክታር ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡ አረሙ እንደበቀለ ካልታረመ እሾህ ስላለው በእጅ ለማስወገድ አስቸጋሪ መሆኑንና በሰው አካል ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ  የጠቀሙት አርሶ አደሩ አረሙ በተደጋገሚ ካልታረመ ከቡቃያ አልፎ የደረሰ ሰብል እንደሚያበላሽ አስረድተዋል፡፡ መጤ አረሙ በእርሻ መሬት ብቻ ሳይሆን በግጦሽ መሬት ላይ በመስፋፋት ለከብቶቻቸው የሚሆን የግጦሽ ሳር መቸገራቸውንም አርሶ አደሩ አስታውቀዋል፡፡ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታምራር ዳኔል በበኩላቸው "አረሙ እንደበቀለ ወዲያኑ ካለታረመ ቡቃያ እንዳያድግ ያደርገዋል" ብለዋል፡፡ የመጤ አረሙ ዘር በቀላሉ እንደማይጠፋ ያስረዱት አርሶ አደሩ አረሙ ተልቶሎ የመብቀል ባህሪ እንዳለውም አርሶ አደሩ ተናግሯል። የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡጉታ ኡኩኝ መጤ አረሙ ቀደም ሲል በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው የክልሉ ወረዳዎች በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱን ተናግረዋል፡፡ መጤ አረሙ በግብርና ልማት ስራው ላይ ትልቅ ተግዳሮት እንደተፈጠረ የጠቆሙት ምክትል ኃላፊው  ቢሮው ከክልሉ የግብርና ምርምር ተቋም ጋር በመቀናጀት ለችግሩ መፍትሄ ለመፈለግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ መጤ አረሙ የቡቃያ ሰብልን ብቻ ሳይሆን የደረሰ ሰብልን ተብትቦ ስለሚይዝና እሾህ ስላለው ለመሰብሰብ አስቸጋሪ መሆኑ ምክትል ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ መጤ አረሙ የክልሉን የማምረት አቅም ከመቀነሱም በላይ 50 ከመቶ በላይ የምርት ብክነት እያደረሰ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ የክልሉ ግብርና ምርምር ተቋም ምክትል ዳሬክተር አቶ ኡጁሉ ሉዋል አረሙ በግብርና ልማቱ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት ተቋሙ ባለፉት ሶስት ዓመታ ባካሄደው የምርምር ስራ ተስፋ ሰጭ ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ ተቋሙ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ከውጭ ሀገር ኬሚካል በማስመጣት በአረሙ ላይ በተካሄደ ሙከራ አረሙ መጥፋት እንደሚችል መረጋገጡን ተናገረዋል። የክልሉ ግብርና ምርምር ተቋም ከቀጣዩ የምርት ዘመን ጀምሮ የአረም ማጥፊያ ኬሚካሉን ወደ አርሶ አደሩ በማድረስ አረሙን የማጠፋት ስራ እንደሚጀመር ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በሳይንሳው አጠራሩ ሚሞሳ በአካባቢያዊ ደግሞ አተንኩኝ ተብሎ የሚጠረው መጤ አረም  በጋምቤላ ክልል መታየት ከጀመረ ከአሰር ዓመት በላይ እንደሆነው ከባለሙያዎች የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም