ስለበዓሉ አመቱን ጠብቆ ከማስተማር ባለፈ የእለት ተእለት ተግባር ማድረግ ይገባል

79
ህዳር 28/2011 የብሄር ብሄረቦችና ህዝቦች ቀን አመትን ጠብቆ ከማክበር ባለፈ እኩልነትን፣ መከባበርንና መቻቻልን ማስተማር የእለት ተእለት ተግባር መሆን እንደሚገባው አስተያየታቸውን የሰጡ መምህራንና ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በትምህርት ቤቶች መከበሩ ተማሪዎች የየራሳቸውን ብሄር ባህል፣ ወግና ባህላዊ አለባበስ  የሚማማሩበት መሆኑን  የተናገሩት በአጸ ፋሲል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስነዜጋና ስነምግባር  መምህር አዳነህ አስረስ ናቸው፡፡ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሲገቡና  በሥራ አለም  ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ስለ ብሔረሰቡ  አስቀድመው ቢያውቁ ለመግባባት እንደማይቸገሩ የገለፁት መምህር አዳነህ  በመከባበርና መፈቃቀር አንድነትን መፍጠር ለሀገር ሰላምና እድገት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ አመትን ጠብቆ  በዓሉን ከማክበር ባለፈ ለተማሪዎችም ሆነ ለህብረተሰቡ ግንዛቤውን የማስረጽ ተግባር በሚፈለገው መልኩ ባለመሰራቱ ያመጣው ለውጥ አነስተኛ ነውም ይላሉ። “በተማሪነት ጊዜያችን እንዲህ አይነት ትምህርት ባለማገኘታችን ከራሳችን ብሄርና ቋንቋ ውጭ ሌላ ያለ አይመስለንም ነበር፤ በስራ አለምም  እስክንለምድ ድረስ ያስቸግራል” ያሉት መምህሩ በበዓሉ አላማ ላይ በመሥራት አሁን የሚስተዋሉ ግጭቶችና የሰላም እጦት እንዳይከሰት ያግዝ ነበር ብለዋል። መንግስት አንድነትን የሚያጠናክሩ የጋራ በዓላትን ከመንደፍ ባለፈ  በሁሉም ዘንድ ሰርጾ  ተግባራዊ እንዲሆን ማስተማርና መደገፍ እንደሚገባ ተየናገሩት መምህር አዳነ ትምህርት ቤቶችም በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት  እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። በአጸ ፋሲል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ኮከበ ብርሌ በዓሉ በትምህርት ቤት ሲከበር የህዝቦች እኩልነት፤ የሀገሪቱ የብሄር ብሄረሰቦችን የአመጋገብና ባህላዊ አለባበስ እንድናውቅ ይረዳናል ብላለች፡፡ “ይህ ደግሞ እኛ ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ ባህልና ወጋችን ሳንረሳ እሴታችንን በማዳበር ጠብቀን በማቆየት ለቀጣዩ ትውልድ እንድናስተላልፍ ያደርገናል” ነው ያለችው ፡፡ በዚሁ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ኡስማን መሃመድ በበኩሉ በዓሉ ሁሉም ዜጎች  አንድ ላይ በመሆን እኩልነትንና አብሮነትን በማስረዳት ሀገራዊ ፍቅር እንዲኖር ይረዳል ብሏል፡፡ “ከታች ጀምረን ስለ ሀገራችን ህዝቦች ማንንት ማወቅ በትምህርት ቆይታችንም ሆነ ወደፊት ወደ ስራ ስንሰማራ ከህብረተሰቡ ጋር ተከባብረን፤ ተቻችለንና ተባብረን በመኖር ለሀገራችን ሰለምና እድገት በአንድነት እንድንቆም ያደርጋል” ብሏል ተማሪ ኡስማን ፡፡ በወይዘሮ ቀለመወርቅ የመሰናዶ ትምህርት ቤት የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ፉአድ አምዱ እንደሚለው በዓሉ በተለይ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ መከበሩ ስለሀገራችን የማወቅ ፍላጎትና ጉጉት በመጨመርና ማንነትን በመረዳት ወደፊትም ጤናማ ግንኙነት  እንዲኖር ይረዳናል ብሏል፡፡ በዓሉ በዘር፣ በጎሳ፣ በብሄርና በሀይማኖት ከመከፋፈል ይልቅ እኩልነትን፣ አንድነትን መተባበርንና በጋራ ሰርቶ ለማደግ ያነሳሳል ያለችው ደግሞ የዚሁ ትምህርት ቤት የአስራ ሁለተኛ  ክፍል ተማሪ ብርሃን ተስፋዬ ናት፡፡ “በሁሉም የትምህርት ክፍለ ጊዜ ስለ እኩልነት፣ መከባበርና ሀገራዊ ፍቅር  ተካቶ ብንማር  መልካም ነው” ብላለች ተማሪ ብርሃን፡፡ በወይዘሮ ቀለመወረቅ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርት አዲስአለም ታዬ በበኩላቸው የበዓሉ መከበር የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች አለባበስና አመጋገብን ከማየት ወጪ በተለይ ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ ፍቅርና የአንድነት ስሜት እንዲኖራቸው ይረዳል ብለዋል። የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ ይከበራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም