በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና በስርቆት ወንጀል የተጠረጠሩ ግልሰቦች በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ

84
አዳማ ህዳር 28/2011 በአዳማ ከተማ በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና በስርቆት ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ግልሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ። የአዳማ ወረዳ ፍርድ ቤት ትናንት በዋለው ችሎት ተከሳሽ ጌታሁን ምትኬ የተባለው ግለሰብ ህዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ አራት ቱርክ ሥሪት ማካሮፍ ሽጉጦችን ከ28 ጥይት ጋር ይዞ ሲንቀሳቀስ በፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋሉን በቀረበለት ማስረጃ መረጋገጡን  አስታውቋል። ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ተከሳሹን ከምሽቱ 1፡30 ላይ በአዳማ ከተማ መልካ አዳማ ቀበሌ ልዩ ስሙ "አሮጌ አዳማ" በተባለ ቦታ በቁጥጥር ስር አውሎታል። የፍርድ ቤቱ ዳኛ ወይዘሮ መሰረት ተሰማ እንዳሉት ፍርድ ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት ግለሰቡ ጥፋታኛ ሆኖ መገኘቱ በማስረጃ በመረጋገጡ በአንድ ዓመት ከስምንት ወር ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ውሳኔ አሳልፏል። "በተመሳሳይ በአዳማ ከተማ ሀንጋቱ ቀበሌ የስርቆት ወንጀል የፈፀመ ግለስብ በሰባት ዓመት ከስምንት ወር ጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል" ብለዋል። ናትናኤል ብርሃኑ የተባለው ይኸው ግለሰብ ህዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ንብረትነቱ የአቶ ዘሪሁን ኩማ የሆነችውን የሰሌዳ ቁጥር 1-4019 (ኦሮ) ባጃጅ ተሽከርካሪ ከቆመችበት ነድቶ ለማምለጥ ሲሞክር በፀጥታ አካላትና በህብረተሰቡ ትብብር በቁጥጥር ሥር መዋሉን በምርመራ ተረጋግጧል። ግለሰቡ በፖሊስና አቃቤ ህግ የቀረበበትን ማስረጃዎች መከላከል ባለመቻሉና ጥፋተኛ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በክስ መዝገብ ምርመራ በማረጋገጡ የቅጣት ብይን ተወስኖበታል። የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሳጅን ወርቅነሽ ጋልሜቻ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ህግ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ወንጀልን በመከላከል በኩል ከመንግስት ጎን ሆኖ እያሳየ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም