ፍርድ ቤቱ በፍጹም የሺጥላ መዝገብ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ሰጠ

425

አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ የወንጀል ችሎት በነፍጹም የሺጥላ መዝገብ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ለመስጠት እና የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ውሳኔ ለመስጠት ለነገ ቀጠሮ ሰጠ።

ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት ትዕግስት ታደሰ፣ጋዜጠኛ ፍጹም የሺጥላና አቶ ቸርነት ዳና ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን ፖሊስ ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ያከናወናቸውን ተግባራት ለፍርድ ቤቱ አቅርቧል።

ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው ትዕግስት ታደሰ በስሟ በርካታ ሐብት የተገኘ ሲሆን በህገ ወጥ መንገድ ያገኘችው ገንዘብ ህጋዊ በማድረግም ተጠርጥራለች።

ትዕግስት ታደሰ ላይ የህብረት ማኑፋክቸሪንግ ማሽን ግንባታ ሦስት ሙያተኞችንና ለተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት የሸጡ ሁለት ምስክሮችን ቃል መቀበሉንና ሌሎች መረጃዎችን ማሰባሰቡን ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

ፖሊስ በተጠርጣሪዋ መኖሪያ ቤት ምርመራ ባደረገበት ወቅት በህገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስለው የሰሯቸው ስራዎች የሚያሳዩ ሰነዶችን ማግኘቱን ገልጿል።

ጋዜጠኛ ፍፁም የሺ ጥላ ላይ ከአራት ሰዎች የምስክር ቃል መቀበሉን፣ ክፍያ እንዲፈፀም የተደረገበት ማስረጃ መሰብሰቡን እና የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን አባል እንዳልሆነች ማረጋገጡን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

በሦስተኛ ተጠርጣሪ በአቶ ቸርነት ዳባ ላይ ሁለት የምስክር ቃል እንደተቀበለ፣ በድለላ የተከፈላቸውን ኮሚሽን መጠን የሚያሳይ ማስረጃ መሰብሰቡን እና ግለሰቡ በስኳር ኮርፖሬሽን ላይ ህጋዊ ፍቃድ ሳይኖራቸው የሰሯቸው ስራዎችን እየመረመረ መሆኑን አስረድቷል።

በአጠቃላይ ተጨማሪ የሰውና ሰነድ ማስረጃ ለማሰባሰብና ሌሎች ግብረ አበሮችን ለመያዝ በሦስቱም ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ በተሰጠው የሰባት ቀን የጊዜ ቀጠሮ ውስጥ እሰራለሁ ያለውን ስራ አላከናወነም፣ ፖሊስ የሚፈልገው ቀሪ ማስረጃ ለማግኘትም ተጠርጣሪዎች ተፅዕኖ አያሳድሩም እና የቀረበባቸው ጉዳይ ዋስትና የማያስከለክል በመሆኑ በዋስ ወጥተው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጠይቀዋል።

ፖሊስ የዋስትና ጥያቄውን የተቃወመ ሲሆን ችሎቱ ፓሊስ በጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲሁም የተጠረጣሪ ጠበቆች የጠየቁትን የዋስትና ጥያቄ ትዕዛዝ ለመስጠት መዝገቡን ለነገ ረፋድ 5 ሰዓት ቀጠሮ ሰጥቷል።

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ከፍተኛ አመራር የነበሩት ዶክተር ሃሺም ቶፊቅ ባለቤት ወይዘሮ ዊዳድ አህመድ ላይ ፖሊስ ባቀረበው ምንጩ ያልታወቀ ሐብት ማፍራት ምርመራ ከእንይ ሪል እስቴት ያገኘውን መኖሪያ ቤት ማሳገዱንና ለተለያዩ ተቋማት ደብዳቤ መጻፉን ለችሎቱ አስረድቶ ተጨማሪ ሰነዶችን ለመሰብሰብ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

የወይዘሮ ዊዳድ ጠበቃ በበኩሉ የፖሊስ ምርመራ ወደ ተለያዩ ተቋማት ደብዳቤ መላካቸውን የሚያመላክት በመሆኑ ይህን ለመሰብሰብ 14 ቀን መጠየቁ አግባብ ስላልሆነ ደንበኛቸው በዋስ ቢወጡ የሚያሸሹት ማስረጃ የለም በማለት ዋስትና ጠይቋል።

ግራና ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ የዶክተር ሃሺም ቶፊቅ ባለቤት ወይዘሮ ዊዳድ አህመድ በ60 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን የተጠረጠሩበት ወንጀል ከባድ በመሆኑ ተጠርጣሪዋ ከአገር እንዳይወጡ የጉዞ ዕግድ ተጥሎባቸዋል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) አዲስ ሰራተኞች ጋር ተመሳጥረው ከሁለት የውጭ ድርጅቶች 2 ሺህ 500 ትራክተር በድለላ በመግዛት ከ15 ሚሊዮን በላይ ለግላቸው አውለዋል ተብለው በተጠረጠሩት አቶ ረመዳን ሙሳ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል።

አቶ ረመዳን ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ትዕዛዝ ለመስጠት ለዛሬ ከሰዓት በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ ይዞ ነበር።

ፍርድ ቤቱም ከህዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በሚታሰብ ጊዜ አቶ ረመዳን ሙሳ ለታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲቀርቡ ውሳኔ ሰጥቷል።