በኢትዮጵያና ጣሊያን መካከል ያለው የምጣኔ ኃብት ግንኙነትን ማጠናከር ያስፈልጋል..ዶክተር ወርቅነህ

341

አዲሰ አበባ ህዳር 27/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ  በኢትዮጵያና ጣሊያን መካከል ያለው የምጣኔ ኃብት ግንኙነትን ማጠናከር ያስፈልጋል አሉ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢማኑኤል ዲልሪን ጋር በሁለቱ አገራትና በአካባቢያዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ያሉት የጣሊያን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲልሪን ለጋዜጠኞች እንዳሉት ምክክሩ በመሰረተ ልማት፣ በወጣቶች ሥራ ፈጠራ፣ በባህል ልወውጥና በአጠቃላይ የልማት ትብብር ላይ ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በአካባቢው አገራት ያለው ሰላምና መረጋጋት ጠንካራ እንዲሆን እያከናወነ ያለውን “ድንቅ ተነሳሽነት” የጠቀሱት ምክትል ሚኒስትሯ “የጣሊያን መንግስት ለዚህ የኢትዮጵያ ውሳኔ ታላቅ ክብር ይቸረዋል፤ ብዙ ተመክሮም  ይቀስምበታል” ብለዋል።

ይህ የሰላም ሂደት በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ጭምር ከፍተኛ አዎንታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል ሲሉም አክለዋል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት አካባቢ የተረጋጋና የበለፀገ ይሆን ዘንድ ጠንካራ ፍላጎት አንዳለ የተናገሩት የጣሊያን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባለው የተሻለ መረጋጋት ሳቢያ በአገሪቱ ኢንቨስትመንት የመሳተፍ ፍላጎት ያለ በመሆኑ መረጋጋቱ እንዲጠናከር የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለመስጠት አገራቸው ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው በኢትዮጵያና ጣሊያን መካከል ያለው የምጣኔ ኃብት ግንኙነትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።

የጣሊያን ባለኃብቶች መዋእለንዋያቸውን በኢትዮጵያ እንዲያፈሱም ዶክተር ወርቅነህ ጥሪ አድርገዋል።

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ጠንካራ የምጣኔ ኃብት ትስስር እንዲፈጠር የጣሊያን መንግስት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ቃል መግባታቸውንም ዶክተር ወርቅነህ ገልፀዋል።