የአገሪቱን አንድነትና ሰላም ለማስጠበቅ ሁሉም ዘብ ሊቆም ይገባል ተባለ

290

አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተቻችሎ እና ተፈቃቅሮ የመኖር ባህል እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ።

የብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን አስመልክቶ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የተለያዩ ቢሮዎች አመራሮች፣ አባ ገዳዎች እና የአገር ሽማግሌዎች ዛሬ የፓናል ውይይት አካሂደዋል።

የፓናሉ ታሳታፊዎች በዚሁ ወቅት እንዳሉት መንግስት፣ አባገዳዎች፣ ቄሮዎች፣ የተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲዎችና የሃይማኖት ተቋማት በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በጋራ መስራት አለባቸው።

የዜጎች የአብሮ የመኖር እሴቶችን ለመሸርሸር ጥረት የሚያደረጉ አካላት ለህግ በማቅረብ ግጭቶችና መፈናቀሎች መቆም እንዳለባቸውም ተሳታፊዎቹ አሳሰበዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል አቶ ገረሙ ነፈባሳና ቶ ቶለሳ ኪሼ  እንዳሉት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የሚከሰቱ ግጭቶችን በአፋጣኝ በመፍታት የህዝቡን አንድነት ማጠናከር ያስፈልጋል።

ዘላቂ ሰላምና አገራዊ አንድነት እውን ይሆን ዘንድ  የህዝቦችን አንድነት እና ትስስር በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ መንግስት በትኩረት መስራት እንዳለበት ጠቅሰዋል።

የመገናኛ ብዙሃን፣ መንግስት እና የሚመለከታቸው አካላት በአገሪቱ ያሉትን ባህላዊ እሴቶችን በሚያጠናክሩ እና ማቀራረብን በሚያመጡ ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል።

ከኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ወይዘሮ አለሚቱ ዱሬሳ የአገሪቱ ህዝቦች በመካከላቸው ያለውን መቻቻል በማጠናከር ልዩነትን በውይይት በመፍታት የቆየውን አብሮ የመኖር ባህሉን አጠናክሮ የሚቀጥልበትን ስርዓት መፍጠር እንደሚገባ ገልፀዋል።

አባ ጨፌ ጫላ ሶሪ በበኩላቸው በገዳ ስርዓት መሰረት እንኳን ሰውን አውሬን መጉዳት እንደማይፈቀድ ገልጸው “አገራችን በጋራ ማሳደግ አለብን” ብለዋል።

መንግስት ችግሮች ሳይከሰቱ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለበት፣ ችግሮች ከተከሰቱም በኋላ በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት መጣር ይጠበቅበታል ሲሉም አባ ገዳው ተናግረዋል።

በገዳ ስርዓት መሰረት እሳቸውም ከሌሎች አባ ገዳዎች ጋር በመሆን ዘላቂ ሰላም ማምጣት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ እየሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ኦሮሚያ ክልል የጫፌ አፈጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው በብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል፣ የአገሪቱን አንድነትና ሰላም ለማረጋገጥ ህዝቡ እንደከዚህ ቀደሙ በፍቅር መኖር አለበት ብለዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ችግሮችን የሚፈጥሩ እና የሚያባብሱ አካላትን ህዝቡ አጋልጦ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

13ኛው የብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ቀን “በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊነት ለአንድነት” በሚል መሪ ቃል ዘንደሮ የአዲስ አበባ ከተማ በመጪው ቅዳሜ ይከበራል።